የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ_06.05.08
“ መጽሐፍ ቅዱስን ከልክ በላይ ልታነበው አትችልም
ያነበብከው ከሆነም በደንብ አድርገህ አላነበብከውም
በድንብ አድርገህ አንብበኸው ከሆነም በደህና አድርገህ አልተረዳኸውም
በደንብ አድርገህ የተረዳኸው ከሆነም ደህና አድርገህ አላስተማርከውም
በደህና አድርገህ ያስተማርከው ከሆነ መኖር እንደሚገባህ አልኖርከውም ”
ማርቲን ሉተር
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ስድሳ ስድቱ መጻሕፍት እግዚአብሔር በመንፈሱን ባኖረባቸው ቃላት የተሞሉ እንደሆኑ እናምናለን። እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና አነሳሽነት ምንም ስሕተት የሌለበትን የእግዚአብሔርን ቃል እንደጻፈ እናምናለን።
መጽሐፍ ቅዱስ
የስሙ መጠሪያ
መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው መጠሪያ ለመጽሐፍ ቅዱስ ለብቻው የተሰጠ መጠሪያ ነው። በእንግሊዝኛ " ባይብል" የሚለው መጠሪያ በግሪክኛ ለማንኛውም መጽሐፍ የሆነ መጠሪያ ነበር። ቅዱሳት መጻሕፍትን ባይብል በሚለው መጠሪያ መጥራት የተጀመረው ብሉይ ኪዳን በግሪክ ቋንቋ ከተተረጎመበት ግዜ ጀመሮ ነው ማለት ይችላል። ምክንያቱም በትንቢተ ዳንኤል በምዕ. 9፡2 ላይ "… የአመቱን ቁጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ" የሚለውን ለመተርጎም ግሪክኛው ቢቢሊያ የሚለውን የባይብልን የብዙ ቁጥር በመጠቀም እንደጻፈ መጻሕፍት ይናገራሉ።
በ2ኛ ጢሞቲዎስ 3፡15 ላይ "ቅዱሳን መጻሕፍት" የሚለው መጠሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙትን ሁሉ በመጠቅለል የተነገረ አባባል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከአርባ በማያንሱ ጸሐፊዎች በ1400 ዓመታት መካከል በሶስት የተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፈ መጽሐፍ ነው።
2ኛ ጢሞ. 3፡16
“የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።”
መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ተጻፈ?
ቋንቋና የመጽሐፍ ጸሐፊዎች
ስነ ጽሑፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ አኳያ ሲታይ መቼና እንዴት እንዴት እንደተጀመረ የሚናገር ቀጥተኛ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ተዘግቦ አይታይም። ከቅዱሳት መጻሕፍት አኳያ ሲታይ የመጀመሪያው ጸሐፊ ሙሴ እንደነበረ በግልጥ እንመለከታለን። ዘዳግም 31፣9 “ሙሴም ይህችን ሕግ ጻፈ፥ የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳኑን ታቦት ይሸከሙ ለነበሩት ለሌዊ ልጆች ለካህናቱ ለእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰጣት።”
ከሙሴ በፊት የስነጽሑፍ ስራ ከአብርሃም ዘመን በፊት ቀደም ብሎ ተጀምሮ እንደነበረ ታሪክ ይናገራል። ከዚህ በመነሳት በዘፍጥረት ላይ የምናገኘውን ታሪክ አብርሃም በጽሑፍ አስፍሮት ሊሆን ይችላል በማለት የሚገምቱ አንዳንድ ጸሐፊዎች አሉ። አምስቱ የሙሴ መጻሕፍ በሙሴ አማካኝነት እንደተጻፉ ከጥንት የነአሩ አይሁዳውያን ያምናሉ። ከዚያም በኋላ የተገኙት መጻሕፍት ትንቢቶቹ በነቢያቱ አማካኝነት ተጽፈው እንደነበረ ይታመናል።
እብራይስጥና አረማይክና የግሪክ ቋንቋ
ከጥቂቶች ስፍራዎች በስተቀር ከፍተኛው ክፍል የብሉይ መጽሐፍ እንዳለ በዕብራይስጥኛ የተጻፈ ነው። ጥቂቱ ክፍል አይሁዳውያን በባቢሎን ምርኮ ሳሉ በተማርት የባቢሎን ቋንቋ በአረማይ የተጻፈም እንዳለ ይታወቃል።
በብሉይ ኪዳን የሚገኙት ብዙዎቹ ታሪኮች ግጥሞች ቅኔዎች የትውልድ ሐረጎች እንዲሁም የተለያዩ ትናንሽ የጥበበና የምክር ንግግሮች በቃል ታሪክ ከሰው ወደ ሰው ሲንገሩ የቆዩ ሆነው በመጨረሻም በጻፍቶች አማካኝነት በመጽሐፍ ላይ እንዲሰፍሩ እንደተደረጉ ይታመናል።
በአይሁዳውያን መካከል መልክ ባለው ሁኔታ የስነጽሑፍ ስራ በተደራጀ መልኩ የተጀመረው በኑስ ዳዊትና በንጉስ ሶሎሞን ዘመን እንደነበረ ይገመታል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምንድር ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች በልዩ ሁኔታ የገለጠበት መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ እንደ ጸሐፊዎቹ በዘመንና በቋንቋ የማይወሰነው የእግዚአብሔር መጽሐፍ ነው። ስለሆነም በሁሉም መጻሕፍት የሚታየው እንድ የጋራ መልእክት ነው። ይህንን መልእክት በየዘመኑ የነበሩትን የተለያዩ ቋንቋዎች፤ ታሪካዊና ባሕላዊ ሁኔታዎችን እየተጠቀመ ስለ ራሱና ስለ ዘላለማዊ እቅዱ የገለጠው ዓምላክ አንድ በመሆኑ መጽሐፉ የተሳሰረና የተያያዘ ነው። አንዱ መጽሐፍ በሌላው መጽሐፍ ላይ ከተገለጠው እውነት ሳይርቅ ባለው ላይ በመጨመር ወይንም ያለውን በማብራራት ተደጋግፎ የተጻፈ መጽሐፍ ነው። የዚህ መተሳሰርና መያያዝ ምንጩና ምክንያቱ የመጽሐፍ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር ራሱ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ሃሳብ የሚገልጥ መጽሐፍ ነው። ጌታ አምላክ ለሰው ልጆች ራሱን የገለጠበት ሃሳብ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ በጽሑፍ መልክ ለሰው ልጆች ቀርቦአል። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን መገለጥ እንደያዘ መገንዘብ መሰረታዊ የሐይማኖት አቋም ነው። እግዚአብሔር ወደ ለሰው ልጆች ራሱን የገለጠባቸው መንገዶች የቱን ያህል በተለያየ መልካቸው ተዘርዝረው ቢቅርቡም ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ይላ እግዚአብሔር ቃል የሐይማኖት ምክንያት ሊሆኑን እንደሚችሉ ማስብ አስቸጋሪ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ምንነት ስንመለከት የሚከተሉትን ነጥቦች መገንዘብ አለብን፣-
- የመፅሐፍ ቅዱስ ፀሐፊ እግዚአብሔር ነው
i. መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ነው።
ii. እግዚአብሔር ያለና የነበረ አምላክ ስለሆነ በተለያዩ ፀሐፊዎች ተጠቅሞ መጽሐፉን ቢያፅፍም የመጽሐፉ መልእክትም ሆነ የአላማው አንድነት በእግዚአብሔር መንፈስ የተጠበቀ ነው።
የጌታ ቃል በጌታ ፈቃድ የተጻፈ እንጂ በሰው ፈቃድ የተፃፈ አይደለም።
መጽሐፍ ቅዱስን ስናጥና ልናውቀውና ልንረዳ የምንሞክረው እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆችና ለፍጠርት ሁሉ ያለውን ፈቃዱ ምን እንደሆነና ምን ሊያደርግ የሚወደውንም ዓላማውን ለማወቅ ብለን ነው የምናጠናው። መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የእግዚአብሔርን ሃሳብና ፈቃዱን በቀጥታ ለማወቅ የምንችልበት ሁኔታ ላይ እንደምንሆን ማወቅ አለብን።
መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን የቻለ አንድ ሙሉ መጽሐፍ ሆኖ ሊወሰድ ይቻላል። ከዘፍጥረት እሰክ ራዕይ ያለው እያንዳንዱ መጽሀፍ የየራሱ የሆነ ታሪክና መልእክት አለው። መጽሐፉ እንደ ፀሐፊዎቹ በዘመንና በቋንቋ የማይወሰነው የእግዚአብሔር መጽሐፍ በመሆኑ በሁሉም መጻሕፍት የሚታየው አንድ የጋራ መልእክት ነው።
ይህንን መልእክት በየዘመኑ የነበሩትን የተለያዩ ቋንቋዎች ታሪካዊና ባሕላዊ ሁኔታዎች እየተጠቀመ ስለ ራሱና ስለ ዘላለማዊ እቅዱ የገለጸው አምላክ አንድ በመሆኑ መጽሐፉ የተሳሰረና የተያያዘ መጽሐፍ ነው። አንዱ መጽሐፍ በሌላው መጽሐፍ ላይ ከተገለጠው እውነት ሳይርቅ ባለው ላይ በመጨመር ወይንም ያለውን በማብራራት ተደጋግፎ ተጽፈል።
ይህንን መተሳሰር ያመጣው በመጽሐፉ የተነገሩትን እውነቶች ያመነጨው እግዚአብሔር ራሱ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መጽሀፍ ቅዱስን እንዴት ጻፉት?
መጽሐፍ ቅዱስ በከ40 የማያንሱ ጸሐፊዎች በ1600 ዓመታት መካከል የተጻፈ መጽሐፍ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በተለያየ ዘመንና ፤ በሶስት ኮንትኔንትን በሶስት የተለያዪ ቋንቋዎች ሊጽፉ ችለዋል። መጽሐፍ እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች በልዩ ሁኔታ የገለጠበት መጽሐፍ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን የቻለ አንድ ሙሉ መጽሐፍ ሆኖ ሊወሰድ የሚገባብት ትልቁ ምክንያት ። ከዘፍጥረት እሰክ ራዕይ ያለው እያንዳንዱ መፅሀፍ የየራሱ የሆነ ታሪክና መልእክት አለው።
መጸሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት ሁኔታን መጽሐፉን ለመረዳት መግለጫ የሆኑ ቃላትና ትርጉማቸው
- መገለጥ (ሪቬሌሽን) i. ከመጽሐፍ ቅዱስ አኳያ መገለጥ ሰው በተፈጥሮ ሊያውቅና ሊረዳው የማይችለውን እውነት ከእግዚአብሔር የተቀበለበትን መንገድ ያሳያል። በዚህ መገለጥ ሰው ስለ እግዚአብሔር ማንነት ባሕርይና ሕልውና እንዲያውቅ ተድርጎአል። እግዚአብሔር ራሱን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በመግለጥ ማንነቱን ገልጦአል።
ii. የመጽሐፍ ቅዱስ ፀሐፊዎች ይህንን መገለጥ በመገንዘብ ምስክሮች ሆነው እንደጻፉት ሳይሆን የምናምነው በመገለጥ ያወቁትን በመገለጥ ጻፉት በማለት እናምናለን። የመጽሐፉ መጻፍ ራሱ መገለጡን እውን እንዲሆን የሚያደርግ ስራ በመሆኑ መገለጡ ለብቻ መጻፉ ደግሞ የዚያ ውጤት አይደለም። አለበለዚያ ጽሁፉ የሰው መገለጡ የእግዚአብሔር ሆኖ በመወሰዱ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መሆኑ ይቀራል።
a. በዚህ ጉዳይ ሊብራል የሆነ አመለካከት ያላቸው የስነ መለኮት ተማሪዎች የሚከተሉትን አባባሎች ይናገራሉ፣
i. መገለጥ በመንፈስ ቅዱስ የሚሆን በመሆኑ እምነታችን በመጽሐፍ ሳይሆን በመገለጥ በሚታወቀው ክርስቶስ ነው በማለት በመጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃልነቱ ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን እምነት ይጥላሉ።
ii. የመፅሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃልነት ውድቅ በሆነበት በዚህ አመለካከት ሰዎች ለሚያምኑት እምነት ድጋፍ ይሆነናል ብለው የሚቆሙበት የእምነታቸው ድጋፍ የተጣለው በሰው አብርሆተ ሕሊናናን ልምምድ ላይ ሆኖአል።
iii. መገለጡ የመገለጥነት ሂደቱን የፈጸመው መጽሐፉ የተጻፈበትን አጠቃላ ሂደት በመቆጣጠርና ወደ ፍጻሜም በማድረስ ነው። መገለጥ ያለ መጻፍ ለብቻ የሚታይ ሂደት አይደለም። በ2ኛ ጢሞ.3፡16 መሰረት በመጽሐፍት ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ አለባቸው ሲል የመገለጡ ምንጭና ምክንያት የሆነው መንፈስ ቅዱስ መግለጡን ሙሉ ያደረገው በመጽሐፍቱ ውስጥ በመገለጥ ነው እንጂ ከመጽሐፍቱ ተለይቶ መገለጥ በመስጠት አይደለም።
iv. ገላጩን የምናገኘው መገለጡን ባሳየባቸው መጻሕፍት ነው። ስለ ሆነም የገላጩን መገለጥ ለማግኘት መጻሕፍቱን መገናኘት ያስፈልጋል።
v. ጸሐፊዎቹ የተገለጠላቸውን የገለጡት ከገላጩ ተለይተው አልነበረም። ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲፅፉ ገላጩ በጽሁፎቹ እንዲገኝ የሚያደርገው ትልቁ ምስጢር ጽሁፎቹ ያለ ገላጩ ያልተጻፉ በመሆኑ ነው። ከዚህ የተነሳ ነው መጻሕፍት የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መጻሕፍት ተብለው የሚጠሩት።
vi. ከሐዋርያት ዘመን አኳያ ሲታይ ይህ ሁኔታና ከብሉ ኪዳን ነቢያት አኳይ ሲታይ ይህ ሁኔታ ለተሰበከውም ሆነ በጽሑፍ ለቀረበው መንፈሳዊ መልእክት ሁሉ የሚሆን ነው።
vii. ይህ በዚህ መልክ ከተወሰደ ቅዱሳት መጻሕፍት የመገለጥ አስተላላፊ በሆኑ ሰዎች መሳሪያነት የተጻፉ በመሆናቸው የሰዎቹ ባሕርይ የቃላት አጠቃቀማቸው ስሜታቸው ሁሉ የተንጸባረቀበት ሁኔታ ያታይባቸዋል።
viii. በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጡትን ቃላት የመረጠው እግዚአብሔር ነው። በብሉይ ኪዳን ነቢያቱን እንዲህ በሉ ሲላቸው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለው እንዳሉ ጌታ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉትን ቃላትና ሃሳቦች በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ መራጭነትና ተቆጣጣሪንት ጸሐፊዎቹ እንዲጽፉት በሚያደርግ መነሳሳት ተጠቅሞ እንደ ጻፉት እናምናለን።
- መነዳት (መቀስቀስ) (ኢንስፕሬሽን)
v ከመጽሐፍ ቅዱስ አኳያ መነዳት የሚያመለክተው ሰው ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መገለጥ በጽሑፍ ያሰፈረበትን ሁኔታ ያመለከታል።
v በመነዳት እግዚአብሔር የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን ተክለ ሰውነታቸውንና የተፈትሮ ስጦታቸውን ስያዛባና ስያፋልስ እንዲጽፉ የሚወደዳቸውን ቃላት በመጠቀም እንዲጽፉ ያደርገበትን አሰራሩን ያሳያል።
v መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው ቅጂ ምንም ስህተት ሳይገኝበት ደካማ በሆኑ ሰዎች በመጠቀም ስህተት የሌውን እውነቱን እግዚአብሔር እንዲጻፍ ያደርገበትን መንገድ ያሳያል። በመገለጥ የተቀበሉትን በመነዳት ጻፉት ማለት እንችላለን። (2ኛ.ጴጥ.1፥20-21፤2ጢሞ. 3፥16)
v በመነዳት መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳን ጸሐፊዎች ውስጥ ሃሳቡንና ሃሳቡን ሊገልጡ የሚችሉትን ቃላት ሁሉ ምንም ሳይቀር በእነርሱ ውስጥ አስቀምጧል። ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱን ቃልና አረፈተ ነገር ከስህተት በመጠበቅና በመከላከል እንዲጻፍ ተቆጣጥሮአል። ስለሆነም መጻሕፍቱ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው” መጻሕፍት ናቸው። (2ኛጢሞ.3፥16፤ኤር.1፥9 ፤2ኛ ሳሙ.23፥2፤ ዘፀ.31፥18፤32፥16) እያንዳንዱ ቃልና እውነት እስትንፋሰ መለኮት ያለበት መጽሐፍ ነው።
v የእግዚአብሔር እውነት በቅዱሳን ጸሐፊዎች ውስጥ ሲያልፍ ስብዕናቸውን ሳይሽር ግላዌ ባሕርያቸው ሳይሸፈን፤ ልምዳቸውና የእውቀታቸው መጠን ሳይከለከል ተጠቅሞባቸዋል።
v በመጽሐፍ ቅዱስ ያለው ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል በመሆን የእግዚአብሔርን መገለጥ የየያዘ ሆኖ ነው የተጻፈው። በመሆኑም የመለኮት ቃል ነው (ሮሜ 3፣2)።
- ቃል በቃል የሆነ መነዳት (ፕሌናሪ ቨርባል ኢንስፕሬሽን)
v ይህ ቃል የሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ በመነዳት እንደተጻፈ ነው።
v በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር በመነዳት ቅዱሳንን ያጻፋቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ቃላቶቹንም ጭምር እየነዳቸው እንደሻፋቸው የሚገልጥ እገላለጽ ነው። (1ኛ ጢሞ. 3፡16፤ ማቴዎስ 22፡32)
ጴጥሮስ የእግዚአብሔር ቃል እንዴት እንደመጣ ሲናገር ሶስት መሰረታዊ ነጥቦች ይጠቅሳል፣-
2ኛ ጴጥሮስ 1፣21 “ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”
1. ቅዱሳን ሰዎች
a. እግዚአብሔር የተጠቀመባቸው ሰዎች መንፈሳውያን የሆኑና ለእግዚአብሔር የተለዩ እንደነበሩ ያሳየናል።
b. እነዚህ ሰዎች ከሰው የተገኘ ወይንም በሰው የተቀሰቀሰ ንግግር እንዳልተናገሩ ያሳያል።
2. በእግዚአብሔር ተልከው
a. የአምላክ መልእክተኞች ሆነው የተናገሩት መልእክት እንደነበረ እናያለን።
b. እግዚአብሔር የመልእክቱ ምንጭ እንደነበረ ይታያል።
c. ከሰው ፈቃድ ጋር ያልተያያዘው መልእክት ሊገኝ የቻለው ላኪው እግዚአብሔር ስለ ሆነ እንደሆነ ማይት ይችላል።
3. በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው
a. መንፈስ ቅዱስ ተላኪዎቹ የተላኩትን መልእክት በትክክል እንዲናገሩ እንዳደረገ ይታያል።
b. መንፈስ ቅዱስ በተናጋሪዎቹ ላይ ይሰራ የነበረው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ ሲታይ
Ø በመንዳት
Ø ግድ በማለት
Ø በመቀስቀስ
Ø በመምራት እንደተጠቀመባቸው ይታያል።
c. ግሳዊ መልኩ ሲታይ የማይሻገር ግስ ነው። ነቢያቱ የሚነዱት በሌላ መሆኑ እያሳየ ተነጂ የሆኑበት አቋማቸውን ያጎላል። በመሆኑም ከቶ በሰው ፈቃድ አለመጣምና የሚለውን ተነጂ የሆኑትን ነቢያቱን ራሳቸውን የሚጨምር ሆኖ እናገኘዋለን።
Ø ጳውሎስ እስረኛ ሆኖ ወደ ሮም የሄደባት የነበርችውን መርከብ አውራቂስ የነዳበትን አነዳድ በዚሁ ቃል በመጠቀም ሉቃስ ይናገራል (ሐዋ. 27፣15)።
- የአይነ ልቡና ብርሃን ማግኘት
v ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር የአይነ ልቡና ብርሃን ማግኘት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የተገለጠውንና በመንፈስ ቅዱስ ተቆጣጣሪነት በመነዳት የተጻፈውን የጌታን ቃል ለመረዳት አንባብያን ከመንፈስ ቅዱስ የሚያገኙትን ብርሃን ያሳያል።(ኤፌ.1፥17)
መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው የእግዚአብሔርን መልእክት ነው
v መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በቅዱሳን አድሮ ስለ ራሱ የተናገረው እንጂ ቅዱሳን ስለ እግዚአብሔር ያላቸውን መረዳት ወይንም አስተያየት የገለጹበት መጽሐፍ አይደለም።
v እግዚአብሔር በቅዱሳን ውስጥ በመሆን በታሪካቸው፤ በባህላቸውና በቋንቋቸው በመጠቀም ሃሳቡን በትክክል የሚገልጹ ቃላትን በመምረጥ ስለ ራሱ ማንነትና ስለ ፈቃዱም ይገልጽላቸው ነበር።
v እግዚአብሔር እንዲህ ይላል የሚለው አባባልና አቻው ከ2000 በላይ ጊዜ በብሉይ ኪዳን ተጠቅሶአል (ኢሳ.8፡1,11፤2ሳሙ. 23፤1-፤ኤር.1፥9፤5፥14፤7፥27፤13፥12)። በአዲስ ኪዳን (ዕብ.1፡1፤ማቴ.1፡22፤2፡15፤የሐዋ.1፡16፤)
የእግዚአብሔር ቃል
1. የፀና ቃል 2ጴጥ.1፡19
2. የታመነ ቃል 1ጢሞ.1፡15፤2ኛጢሞ. 2፡11፤ ቲቶ 3፡8
3. ዘላለማዊ ቃል 1ጴጥ. 1፡24
4. የተረጋገጠ ዕብ.2፡3
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የጌታ ኢየሱስ አመለካከት
1. ማቴ 5፡18
2. ማር. 7፡13
3. ዮሐ. 10፡35
4. ሉቃ. 16፡31
5. ሉቃ. 24፡27
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሐዋርያት አቋም
1. ጴጥሮስ
Ø 2ኛ ጴጥ.1፥20-21
2. ጳውሎስ
Ø 2ጢሞ.3፥16
1. ለብሉይና ለአዲስ ኪዳን
1ኛ. ቆሮ. 2፥12-13
በመገለጥ የመጣ
በመገለጥ የተጻፈ
2. ለሐዋርያት ትምሕርትና ስብከት
Ø 1ኛ ቆሮ.14፡37
Ø 1ኛ ተሰ. 2፡13
መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እናነባለን ?
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ከማንኛውም መጽሐፍ በላይ በአክብሮትና በጥንቃቄ መነበብና መጠናት ያለበት መጽሐፍ ነው። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ውጤት በሚያመጣ ሁኔታ እንዴት ማንበብ እንዳለባቸው አያውቁም። ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት አላቸው ነገር ግን በውስጡ የተቀመጠውን ሐብት ቆፍረው ለማውጣት ግዜ አይሰጡትም። ብዙ አማኞች አዲስ ኪዳንን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ አንብበው አያውቁም። በጣም ጥቂት የሆኑ አማኞች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በዓመት አንድ ግዜ አንብበው ለመጨረሽ ችለዋል። እርግጠኛ ነኝ የሙሉ ግዜ አገልጋዮች ከሚባሉት መካከል መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በአመት አንድ ግዜ ያህል የማያነቡ ሞልተዋል። ብዙ አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ ይልቅ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉ መጻሕፍትን በማንበብ ግዜያቸውን ያጠፋሉ።
መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያነቡት መካከል መልክና አግባብነት ባለው ስርዓት የሚያጠኑት በጣም ጥቂቶች ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ስናደራጅ ልናደርገው የሚገባ ትልቅ ነገር አማኞች የጌታን ቃል ስርዓት ባለው ሁኔታ እንዲያነቡት ማድረግ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንደ ስሙ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ያተኮረ ጥናት መሆን ይገባዋል። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ አማኞች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በግልም ሆነ በግሩፕ ሲያጠኑ ሊጠቅማቸው የሚችለውን መሰረታዊ የአጠናን ዘዴ እንዲያገኙ የሚረዳ ነው።
ቤተ ክርስቲያኒቱ ራዕይዋን ተግባራዊ የምታደርግበት አንዱ መንገድ መጽሐፍ ቅድስ በእያንዳንዱ አማኝ ሕይወት ሊኖረው የሚገባውን ስፍራ እንዲይዝ በማድረግ ነው። ያለ ጌታ ቃል የክርስትና ሐይማኖት ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው ሐይማኖት ሆኖ የሚያኖረው ምንም ምሰረት የለውም።
ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን የሚያነቡባቸው የተለያዩ ሁኔታዎች አሉ ከነዚህ መካከል የሚከተሉት ጎልተው ያታያሉ ፡-
v መፅሐፍ ቅዱስ ሳይገባቸው እንዲሁ በማንበብ ብቻ የሚገኘውን በረከት እንደሚቀበሉ የሚያምኑ አሉ
v አልፎ አልፎ በገጠመኝ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ
v በፍቺ መጻሕፍት ብቻ በመደገፍ የሚያነቡ
v ላሉበት ሕይወት የሚረባ ነገር ብቻ ለማግኘት የሚያነቡ። ችግራቸው የሚያስነብባቸው።
v መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሎተሪ እየገለጡ በድንገት የወጣውን ስፋራ የሚያነቡ አሉ።
v በብልሃት ትክክለኛ የአጠናን ዘዴ በመጠቀም የሚያነቡ አሉ።
አማኞች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ለምን ያጠናሉ?
1) ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን እንዲድኑ ዮሐ.20፥30-31
2) ራሳቸውን ማወቅ እንዲችሉ ያዕ.1፥22-25
3) እምነት እንዲሆንላቸው ሮሜ 10፥14-16
4) በፈተና ጊዜ ሐይል ለማግኘት መዝ.119፥11
5) ምሪት ለማግኘት መዝ.119፥105
6) ለበጎ ስራ ለመዘጋጀት 2ጢሞ.3፥16-17
7) ለመንፈሳዊ ውጊያ የጦር እቃ እንዲሆንላቸው ኤፌ. 6፡17
8) በመታነጽ ሰማያዊ ርስትና ለመውረስ የሚያበቃ ጸጋ ለመሞላት የሐዋ. 20፣32
መጽሐፍ ቅዱስና አንባቢዎች
በመጽሐፍ ቅዱስና በአንባብያን መካከል ድልድይ ካልተሰራ በስተቀር ሃሳቡን በቀጥታ ለመረዳት የሚያስቸግር የግንኙነት ገደል አለ። ዋና ዋናዎቹ የግንኙነት ገደሎች የሚከተሉት ናቸው፡-
1) የቋንቋ ገደል
2) የባህል ገደል
3) የመልክዓ ምድር ገደል
4) የታሪክ ገደል
የቋንቋ ገደል
የመጀመርያው መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በጥንታዊ ዕብራይስጥ፣ በጥንታዊ አረማይክና (የከለዳውያን ቋንቋ) በጥንታዊ የኮይኔ ግሪክ ቋንቋ ነበር። እነዚህ ቋንቋዎች ጥንታዊ ከመሆናቸው የተነሳ ዛሬ ለመግባቢያ ሰው የሚጠቀምባቸው አይደሉም።
የቋንቋውን ገደል ማጥበብ የሚቻለው ጥንታውያኑን ቋንቋዎች በማጥናት ብቻ ነው። ይህንን መሰል ጥናት ለማድረግ ብዙ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ለሁሉም ሰው የሚመች ጥናት አይደለም። የቋንቋው ጥናት የሚያተኩርባቸው ሶስት ዋና ዋና ጥናቶች የሚከተሉት ናቸው ፡-
1) የቃላት ፍቺ (ቮካቡላሪ)
2) የሰዋሰውና (ግራመር)
3) የስነጽሁፉ ዓይነት (ጀንሪ)
የቃላት ጥናት (ሞርፎሎጂካል ጥናት)
የአንድን ዐረፍተ ነገር ትርጉምና ሃሳብ ለመረዳት ሐሳቡ የተገለጸባቸውን የቃላት ፍቺ ማወቅ ተገቢ ነው። የቃላት ጥናት የሚያተኩርባቸው አራት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው ፡-
1) የቃሉ አመጣጥ ታሪክ (ሞርፎሎጂ)
2) አንድ ቃል በምንባብ ውስጥ ካሉት ሌሎች ቃላት ጋር ያለው ግንኙነትና መያያዝ (ሲንታክስ)
3) የቃላት ማወዳደር ጥናት (የዕብራይስጥ ቅላትንም ሆን የግሪክ ቅላቶችን ፍቺ)
4) የቃሉ ባሕላዊ ፍቺ (የቃሉ ባለቤት በሆነው ሕብረተሰብ የሚኖረው ትርጉም)
5) በተቀራራቢ ቋንቋዎች የተመሳሳይ ቃላት ፍቺ
ቃላት በጽሕፈት አንድ ሆነው በድምጽ የሚለያዩ ሲሆኑ የተለያየ ትሩም ማምጣታቸውን በጥንቃቄ ማየት ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ በቆሮንቶስ 11፡27 ላይ “ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ …” የሚለው ቃል በአማርኛ ትርጉም ላይ ብቻ ከተወሰደ ሁለት አይነት መልክ ይይዛል። ስያረዳና ወይንም የማይገባው ሆኖ ሳለ የሚል ትርጉም ይይዛል። ትክክለኛው የትኛው መሆኑን ለመረዳት ከተቻለ በኋላ አነባባችን የቃሉን ትርጉም የጠበቀ ሊሆን ይገባል።
የሰዋስው ጥናት
የሰዋስው ጥናት የተደረገባቸው ቃላቶች አንድ አረፍተ ነገር ለመስራት እንዲችሉ የሚያደርጋቸው የአቀማመጥ ሕግ ከቋንቋ ቋንቋ ይለያያል። የዕብራይስጥና የአማርኛ ቋንቋ ቃላቶች በአንድ አረፍተ ነገር ውስጥ የሚቀመጡበት አቀማመጣቸው ቅደም ተከተል አላቸው። የቃላቱ አቀማመጥ ሲዛባ ትርጉሙ ሊዛባ አረፍተ ነገሩም ጣእም የለሽ ሊሆን ይችላል። ስለሆነም በአንድ አረፈተ ነገር ውስጥ ቃላት የሚቀመጡበት ስፍራ ቃላቱ የሚሰጡትን ትርጉም ይወስናል።
በአንጻሩ የግሪክ ቋንቋ ግን ቃላቶቹ ከሚቀመጡበት የአቀማመጥ ቅደም ተከተል ይልቅ በቃላቶቹ መጨረሻ ላይ የሚጨመሩት ፊደላት ለትርጉም ወሳኝነት ይኖራቸዋል።
1. የአረፍተ ነነገሩ ባለቤት ማን ነው? ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የጥየቀው ጥያቄ ነው? “እባክህ ለቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ?”
2. ድርጊትን ገላጭ የሆኑት ግሶች መልእክቱን በትክክል ለመረዳት የሚኖራቸው ስፍራ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም።
a. ተግባሩ የተገለጠበት ግዜ
b. ግሱ ተሻጋሪ ግስ ነው ወይንስ የማይሻገር ግስ?
c. አዋጅ ነው ወይንስ ትዕዛዝ
3. በግስ የተገለጠው ድርጊት ካለ ድርጊቱን ተቀባይ ማን ነው?
4. በአረፍተ ነገሩ ውስጥ የተገለቱ ቅሽሎችና ድርጻቸውን ማስተዋል?
5. ተውላጠ ስሞች የሚገልጡት ማንን እንደሆነ በጥንቃቄ ማየት?
6. አያያዦችን በተለያየ መልካቸው መረዳት
የስነ ጽሑፍ ዓይነት
አንድን ስነ ጽሑፍ በትክክል ለመረዳት የጽሑፉን ዓይነትና አቀራረብ መመልከት አለብን። አንድ መጽሐፍ ወይንም ስነ ጽሁፍ ሶስት አይነት አቀራረብ (በቕቦቃ ተቶ ዘtኅባቅ ) ይኖረዋል።
1) ታሪካዊ አቀራረብ (ሂስቶሪካል)(Narative / Historical)
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጸሐፊዎች በሚጽፉት ታሪክ ላይ የሚያተኩሩት ሊያስተላለፍ የወደዱትን መልእክት ለመግለጽ የሚመች ሆኖ ባገኙት ጉዳይ ላይ ብቻ ነው።
2) ግጥማዊ አቀራረብ (ፓኤቲክ)(Poetry)
የብሉይ ኪዳን ግጥሞች ጎን ለጎን በሚነጻጸሩ የተለያየ ቃላ የሚቀርቡ ናቸው። ገጣሚው ወይንም ባለ ቅኔው ሃሳቡን ተጭኖ ለመናገር ሲፈልግ የተለያዩ ቃላትን ይጠቀማል።
3) ምሳሌያዊ (Proverbs)
በብሉይ ኪዳን የማንገኛቸው ምሳሌዎች ከሕይወት ተመክሮ የተገኙ ምክሮች ናቸው። ለዕለት ሕይወት የሚጠቅም መመሪያና ምክር በመለገስ መነፈሳዊ ሕይወታችን በጥበብና በማስተዋል እንድንመራ ይረዱናል።
4) ደብዳቤ (Letters)
በአዲስ ኪዳን የምናገኛቸው ደብዳቤዎች ሐዋርያት በነበሩበት ዘምን የሚታየውን የደብዳቤ አጻጻፍ ዘይቤ ጋር የመሳሰላሉ። በደብዳቤ መልክ የተጻፉት ጽሁፎች ለግለሰብ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ወይንም ለብዙ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት የሚጻፉ ሊሆኑ ይችላሉ።
o ለግለሰብ
§ 1ኛ ጢሞቲዎስና 2ኛ ጢሞቲዎስ
§ ቲቶና ፊሊሞና
o ለአንድ ቤተ ክርስቲያን
§ 1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት
o ለተበተኑ አማኞች
§ የጴጥሮስ መልእክቶች
o በርከት ላሉ ቤተ ክርስቲያናት
§ የቆላስያስ መልእክት
§ የራዕይ መልእክት
5) ትንቢታዊ (Apocalyptic)
ሌመጣ ስላለ ነገር የሚናገር ያልተፈጸመ ትንቢት ተምሳሊታዊ (ፊገሬቲቭ) አቀራረብ እስከሌለው ድረስ ታሪካዊነትን በጠበቀና የሰዋስው ሕግን በተከተለ የአተረጓጎም ዘይቤ መተርጎም አለበት።
6) ተምሳሊታዊ (Parables)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ብዙ ያስተምርና ያናገር ነበር። ምሳሌያዊ በሆነ መልክ የሚቀርበው ትምሕርት አንድ ወይንም ሁለት የሆኑ እውነቶችን የማስተላለፍ መልክ ይይዛል። በምሳሌ የተነገረውን ዝርዝር ሁኔታ በተግባር ለማዋል በሚሆን መልክ እኝጠቀም በማለት አክርረን ሁሉንም መውሰድ አይኖርብንም።
7) ተራዛሚ ተለዋጭ (Allegorical)
የስነጽሁፍ አገላለጽ (ሊተራሪ ኤክስፕሬሽን)
እነዚህ ከላይ የተገለጹት በጽሑፍ የሚገለጹበት አገላለጽ (ኤክስፕሬሽን) የሚከተሉትን የስነ ጽሑፍ አቀራረብ አይነቶች በመጠቀም ሲቀርቡ ይታያል።
1) ተነጻጻሪ (Simile) እንደ (like or as)
1ኛ ጴጥ. 1፣24 “ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤
2) አምሳያ / ጥላ (Type)
3) ተለዋዋጭ (Metaphor) A comparison not uning “like” or “as”
ኢሳ. 40፣6 “ጩኽ የሚል ሰው ቃል፤ ምን ብዬ ልጩኽ? አልሁ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው።”
4) አንድን ነገር አጋኖ መናገር (Hyperbole)
5) ግዑዝ የሆኑትን ፍጥረታት እንደ ሰው አድርጎ በመቁጠር የሚቀርብ መልእክት (Personification)
ኢሳ. 55፣12 “እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልልታ ያደርጋሉ፥ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ።”
6) እግዚአብሔርን እንደ ሰው ያለ አካል ወይንም ባሕርይ እንዳለው አድርጎ መቁጠር (Anthropomorphism)
መዝሙር 8፣3 “የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፥ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፥”
7) የእግዚአብሔርን ጥበቃ ወይንም ማዳን በእንስሳ ባሕርይ መግለጥ (Zoomorphism)
መዝሙር 91፣4 “በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል።”
ቀጥተኛ ገለጻ ነው። እንደ እያለ አይናገርም። “ዶሮ ጫጩቶችዋን እንደምታቅፍ” አይነት አይደለም
ምሳሌያዊ አነጋገር እንዴት ይለያል?
የሚከተሉት ጥቅሶች እንዴት መወሰድ አለባቸው?
Ø ሉቃስ 14፣36
Ø ፊሊጵስዩስ 3፣2
Ø 1ኛ ቆሮ. 4፣8
8) ተምሳሊታዊ (ፓራብል)
9) ተራዛሚ ተለዋጭ (አሌጎሪካል)
10) መዝሙራት (ሳልምስ)
11) እንቆቅልሻዊ (ሪድልስ)
12) ምሳሌ (ፕሮቨርብስ) የተጨመቀ ሃሳብ ምክር
13) አምሳያ (ታይፕ) ጥላ
14) ተለዋዋጭ (ሜታፎር)
15) ትንቢታዊ
16) ራዕይ
ተምሳሊታዊ አነጋገር (ፊገርስ ኦፍ ስፒች)
አንድ ጸሐፊ በአንድ መጽሐፍ ውስጥ የሚጠቀምባቸው ቃላትም ሆኑ አረፍተ ነገሮች በዘመኑ ሰዎች ከሚጠቀሙባቸው ግልጽ የአጠቃቀም ዘዴ በወጣና በተለየ መንገድ ሊጠቀም ይችላል። ተምሳሊታዊ አነጋገር ቃላቶችን ወይንም የንገርን መጠሪያ ግልጽ ባልሆነ ስውር መልክ በመጠቀም በአንባብያን ሕሊና ስዕላዊ ዕይታ ለመፍጠር ተብሎ ስነጽሑፉን ሕያው በማድረግ ውበት ሰጥቶ የሚገለጽበት መንገድ ነው።
ተምሳሊታዊ አነጋገርን ለመፍታት ሁለት መሰረታዊ ነጥቦች መታወቅ ያለባቸው ሁለት መሰረታዊ ነጥቦች ይሚከተሉት ናቸው፡-
- ተምሳሊታዊው ንግግር የተገለጸበትን ነገር አስመልክቶ ትክክለኛ ግንዛቤ ይኑርህ።
ለምሳሌ
በሉቃስ 13፥32 ጌታ ኢየሱስ “እንዲህም አላቸው፡- ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ ፡- እነሆ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችን ም እፈውሳለሁ ፥ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት” አለ።
የዚህን ትርጉም ለመመልክተ ስለ ቀበሮ ምንነትና ባሕርይ ማጥናት ይኖርብናል።
- ሁለተኛው መሰረታዊ ነጥብ በተምሳሊቱና ተምሳሊቱ ስለ ሚወክለው ነገር ሊኖር የሚችለውን ግንኙነት ማወቅና መለየት ይገባናል።
v ሄሮድስ በምን አይነተ ሁኔታ ነው ቀበሮን የሚመስለው? ቀበሮ የሚኖራት ባሕርይና ጠባይ ሁሉ ሄሮድስ ሊኖሩት አይችሉም። ከቀበሮ ባሕርያት የትኛው ነው ከሄሮድስ ጋር የሚገናዘበው?
ተምሳሊታዊ አነጋገሮች በምጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ መልክና አይነት ተገልጸዋል። ከዚህ በታች አንድ አስሩን አይነት በዝርዝር እናያቸዋለን።
1) እግዚአብሔርን አካላዊ በሆነ ቋንቋ መግለጽ (አንትሮፖሞርፊዝም)
በዚህ አገላለጽ እግዚአብሔር እንደ ሰው አካል ያለው ሆኖ ተገልጾአል።
መዝሙር 8፥3
ኢሳይያስ 65፥2
2) ቃላትን ሐረግን ወይንም ሃሳብን በማስቀረት መጻፍ (ኢሊፕሲስ)
v ፀሐፊዎች ይህንን የሚያደርጉት ስሙ ሳይጠቀስ ከዐረፍተ ነገሩ ግልፅነት የተነሳ ብቻ ጎልቶ መታየቱን ለመጫን የሚጠቀሙበት መነገድ ነው።
o ለምሣሌ
የባሕል ገደል
በመጽሀፍ ቅዱስ ያሉ መጻሐፍት በሙሉ በአንድ ዓይነት ባሕል ውስጥ የተጻፉ አይደሉም። የተለያዩት ጸሐፊዎች በኖሩባቸው ዘመናት ይኖሩበት ከነበረው አገር በተጨማሪ የሌሎች አገሮች ባሕል በተለያየ ምክንያት ተጽዕኖ ሊያደርግባቸው በሚችልበት ሁኔታ ላይ ነበሩ። የሙሴ መጻሕፍት የሚያንጸባርቁት ባሕላዊ ገጽታ ከግብጽ ኑሮ ጋር የሚያያዝ ሊሆን ይችላል። የኢያሱና የመሳፍንት የከነአንን አካባባቢ ባህል ሊያንጸባርቅ ይችላል። በጠቅላላው በቅኝ ግዛትም ሆነ በስደት ምርኮ ሆኖ በመወሰድና በመሳሰሉት ምክንያቶች በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ባሕሎች ተንጸባርቀው እናገናለን።
የባሕል ግድግዳን ስንመለከት ሁለት ዋና ዋና ባህላዊ ነገሮችን እንመለከታለን።
ቁሳዊ ባሕል (ማቴሪያ ካልቸር)
በእነዚህ ስር የምናያቸው ቤቶችን ፣የምግብ ማብሰያ እቃዎችን፣ምግብና መጠጦችን፣ልብሶችን፤የግብርና መሳሪያዎችን ፣የጦር መሳሪያዎችን፣የመጓጓዣ ዘዳዎችን፣እንስሳትን ፣ይስነ ጥበብ ውጤቶችንና ሐይማኖታዊ ቁሳቅስን ይመለከታል።
ማሕበራዊ ባሕል (ሶሻል ካልቸር)
መጽሐፍ የተጻፈለትን ሕበረተሰብ በደንብ ለመረዳት ከተፈለገ በዚያ ሕበረተሰብ ነገሮች እንዴት እንደሚደረጉና ይሐብረተሰቡ አባላትም እርስ በርሳቸው እንዴተ እንደሚገናኙና ኑሮአቸውን እንዴት እንደሚኖሩ ማወቅ ያስፈልግል። በአንድ ሕብረተሰብ ውስጥ ሰዎች ቤተሰባቸውን ፣ የኢኮኖሚ አያያዛቸውን ፤ የመከላከያ ሐይላቸውንና ፍትሐዊ የአስተዳደር ስርአታቸውን መረዳት ለምናነበው ጽሑፍ ትክክለኛ መረዳትና ፍቺ ይረዳል።
በዚህ ስር አመጋገብ አለባበስ የማጀትና የአደባባይ የኑሮ ባሕልን መገንዘብ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው።
በተጨማሪውም የሰርግና የሐዘን ስራዓትና ወጎችን መመልከቱ ለምናጠናው ጥናት በጣም ተቃሚነት አለው።
ታሪካዊ ገደል
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የኖሩባቸው ዘመንና ጊዜያት በጣም ረጅምና የተለያየ ከመሆኑ የተነሳ አንባቢው ብዙ እርቀት ይኖረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በ1600 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተጻፈ መጽሐፍ ነው። በነዚህ ግዜያት በያንዳንዱ መጽሕፈ ውስጥ የተጠቀሱትን ታሪካዊ ገጽታዎች ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። የታሪክ መጻሕፍትንና የነቢያት መጻሕፍትን አቀናጅቶ ካላጠኑ ትንቢቶችን ለመረዳት አስቸጋሪ ነው። ከዚህም ባሻገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ ተጽፈው የማይገኙ ታሪኮች መታወቃቸው መጻሕፍትን ለመረዳትም ሆነ ትንቢቶችን በትክክል ለመፍታት የሚያስችል ወሳኝ እገዛ የሚያደርግ እውቀት ነው። ታሪካዊ ገደል እንዲጠብ መጽሐፍ ቅዱስ በሚጻፍበት ወቅት ይካሄዱ የነበሩትን ታሪካዊ ሁኔታዎች ከአራት አቅጣጫ ማወቅ ይኖርብናል።
v ጽሑፉን እንዲያነቡ የተጻፈላቸው የመጀምሪያዎቹ እንባብያን እነማን ናቸው?
a. በምን ሁኔታ ላይ ነበሩ?
b. የነበሩብት ታሪካዊ ሁኔታ በተቻለ መጠን መረዳቱ ትልቅ ድርሳ አለው።
v የፖለቲካ ታሪክ
a. ትንቢተ ዮናስ 2፡1-13 መሰረት ዮናስ ወደ ነነዌ ሊሄድ ያልወደደበት ፓለቲካዊ ምክንያት ምንድር ነበር?
በዚህ ስር ሊታሰቡ የሚገባቸው ነጥቦች፦
ምንባቡ በሚያገልጠው ታሪክ ዘመን የነበሩት መሪዎች እነማን ናቸው?
ለሚከተሉት ጥቅሶች ሊታሰብ የሚገባው ፖለቲካዊ ምክንያት ምንድር ነው?
· ሆሴ. 12፡1
· ማቴ. 20፡21
· ሐዋ. 1፡6
v የኢኮኖሚ ታሪክ
አሕዛብ ክርስቲያኖችና አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የተያያዙበት ሁኔታ ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ ነው። ሐዋ. 11፥27-29
ገንዘብ በሚጠናው ምንባብ ተጠቅሶ ከሆነ የተጫወተውን ሚና ተመልከት
በሩት 4፡7-8 ላይ ቦኤዝ ጫማ ለምን ተሰጠው?
በኤፌሶን 1፡14 ላይ መያዣ ማለት ምን ማለት ነው?
v የሐይማኖት ታሪክ
ዘሌዋውያን ላይ ያለው ሕግ የከነአናውያንን አምልኮ እግምት ውስጥ በማስገባት መታየት የሚገባው ሕግ ነው። ዘሌ. 18፡9-14፤ ሐዋ. 19፡24-41
የመልክዓ ምድር ገደል
በመጽሐፍ ቅዱስ ፀሀፊዎችና በአናብቢው መካከል ያለው የመልክዓ ምድር ልዩነት መታሰብ አለበት። ፀሐፊዎቹ የተ ሆነው መጻፋቸው ጽሁፋቸውን ለመረዳት አይነተኛ ሚና ይጫወታል። ጥንታውያን የሆኑት ጽሁፎች የተጻፉባቸው አንዳንዶቹ ከተሞች ዛሬ የሉም።
የጂኦግራፊ ገደል አንድ ጽሁፍ ለመረዳት ከሚያመጣቸው ችግሮች መካከል ለምሳሌነት የሚጠቅመው “በለሰ ስታቆጠቁጥ በጋ ያንግዜ እንደቀረበ ታውቃላችሁ” የሚለው አባባል በትክክል ለመረዳት የሚቻለው እኛ ኢትዮጵያውያን ከለመድነው ሁኔታ በተለየ የወራትና የአየር ለውጥ ባለው ሐገር በበጋ ቅጠሎች እንደሚለመልሙ በክረምት ደግሞ እድነሚረግፉ መረዳት ከቻልን ነው።
የጂኦግራፊ ሁኔታ በሶስት መልክ ሊታይ የሚችልበት ሶስት አይነት መልክ አለው።
የጂኦግራፊ ሁኔታ ሊታይ የሚችልበት ሶስት አይነት መልኮች አሉት። እነርሱም ፦
- የፖለቲካ ጂኦግራፊ
- የጆኦሎጂካል ጂኦግራፊ
- የእጸዋትና የእንስሳት ጂኦግራፊ
አውድ (ኮንቴክስት)
ትርጉሙ
አውድ የሚለው ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ አኳያ ሲታይ የሚያመለክተው አንድ ሃሳብ ከታየበት ጥቅስ ፣ ሞዕራፍ ፣መጽሐፍ ወይንም ከአጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተሳሰረብትንና የተያያዘበትን ሁኔታ ያመለክታል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ያለው እውነት የተያያዘበት ምክንያት ከሁለት ነገር የተነሳ ነው። የመጀመሪያው ከእግዚአብሔር በቀጥታ በተገኘ መገለጥ መጻፉ ነው። ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው በብሉይ ኪዳን ኤርምያስ እግዚአብሔር ስለሚያመጣው አዲስ ኪዳን መናገሩ ነው (ኤር.31፥31-34)።
በሁለተኛ ደረጃ ፀሐፊዎች በእግዚአብሔር መንፈስ እየተነዱና እየተመሩ ቀደም ብሎ የተገለጸውን መገለጥ በመመርኮዝ ከአዲሱ መገለጥ ጋር አስተሳስረው መጻፋቸው ነው። ይህንን በተመለከተ በአዲስ ኪዳን ያለውን አዲስ መገለጠ ከብሉይ ኪዳን ጋር በማያያዝ ማየታችን ይህንን ያሳየናል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በዕብ. 1፥4-14 ያለውና በሮሜ 3፥9-18 በምሳሌነት የሚታይ ይሆናል።
መጽሐፍ ቅዱስ አንድ መጽሐፍ ሆኖ ካልተወሰደ በትርጉም ብዙ ስህተት ሊፈጸም ይችላል። ምንም እንኳን እያንዳንዱ መጽሐፍ በተለያየ ጊዜና ወቅት የተጻፈ ቢሆንም የመጽሐፉ ባለቤትና ዋነኛው ተራኪ እግዚአብሔር የመጽሐፉ አንድነት ጠባቂ ነው። ለአባቶቻችን በተለያየ አይነትና ጎዳና የተናገረው በዘመን መጨረሻም በልጁ የተናገረው እርሱው በመሆኑ ሃሳቡ ሳይፋለስ በተያያዘ መልኩ ለእኛም እንደተናገረ እናምናለን። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት ዘመን፣ ቋንቋ ፣ባህልና ታሪክ የቱንም ያህል የተለያየ ቢሆንም የማይፋለሰውን የእግዚአብሔርን ሃሳብ ከዘፍጥረት ጀምሮ እሰከ ራዕይ እያደገ በሚሄድ መገለጥ የያዘ መጽሐፍ ነው።
የቱንም ያህል የተራራቁ ቢመስሉም ከየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚወሰዱ ጥቅሶች ለብቻቸው የሚያስተላልፉት ሙሉ እውነት ቢኖራቸውም ከአጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተፋለሰ ወይንም ባልተዛመደ ሁኔታ ብቸኛ መገለጥ አይኖራቸውም።
የአውድ ደረጃ
1. የአንድ ጥቅስ አውድ ጥቅሱ የሚገኝበት አንቀጽ ነው።
2. የአንድ አንቀጽ አውድ አንቀጹ የሚገኝበት ምዕራፍ ነው።
3. የአንድ ምዕራፍ አውድ ምዕራፉ የሚገኝበት መጽሐፍ ነው።
4. የአንድ መጽሐፉ አውድ መጽሐፉ የሚገኝበት ኪዳን ነው።
a. አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለመረዳት በውስጡ ያለውን ሃሳብ በአግባቡ ለማየት እንድንችል ሃሳቡ የተገለጥበትን ኪዳን ማጤን አስፈላጊ ነው።
b. ብሉይና አዲስ ሁለት የተለያየ የኪዳን ይዘት አላቸው። ብሉይ ኪዳን በሕግ ላይ ያተኩራል። አዲስ ኪዳን በፀጋ ላይ ያተኩራል።
c. ብሉይ ኪዳን በጥላነት የሚያሳያቸው በአዲስ ኪዳን በአካልነት ተገልጸዋል።
d. በብሉይ ኪዳን ተስፋ የነበረው በአዲስ ኪዳን የተፈጸመ ሆኖአል።
e. አዲስ ኪዳን ብሉይን ይፈታል።
ለምሳሌ ያህል ዘዳግም 6፣25 እና ሮሜ 3፣20 ን እንመልከት።
እነዚህ ሁለት ጥቅሶች እርስ በርሳቸው ይጋጫሉ። የትኛው ትክክል የትኛው ስህተት መሆኑን መወሰን የምንችልበት መንገድ በተገለጡበት ኪዳን የምናያቸው ከሆነ ብቻ ነው። የኪዳንን አውድነት ሳንጠብቅ መጽሀፍ ቅዱሳችንን ብናጠና የምናጠናውን ክፍል ያለ ኪዳኑ በመመልከታችን የተዛባ ትምሕርት ላይ እንወድቃለን።
ብሉይ ኪዳን በኪዳኑ ስር የነበሩት ሕዝበ እስራኤል በሚነጋገሩበት ቋንቋ ተጽፎአል። አዲሱ ኪዳን ለስጋ ለባሽ ሁሉ የሚነገረውን ይወንጌል መልእክት የሚያስተላልፈው በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ይናገሩት በነበረ የመግባቢያ ቋንቋቸው በግሪክ ቋንቋ ተጽፎአል።
5. የአንድ ኪዳን አውድ አጠቀላይ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ወጥ ሃሳብ የተያያዘ መጽሐፍ ነው። ሐዋርያት አይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰውም ልብ ያልታሰበውን ጌታ ገልጦላቸው እንደምተናገሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በሐዋርያት የተነገረው የአዲስ ኪዳኑ መገለጥ ብሉይን ተንተርሰው የተገለጠላቸውን ከብሉይ ኪዳን ጋር አስማምተውና አጣጥመው እንደተናገሩት እናያለን እንጂ አዲስ ኪዳን ከብሉይ በሃሳብ የተለያየና የተፋታ ሆኖ አልተሰበከም አልተጻፈምም። (1ኛ ቆሮ. 2፣13)
መጽሐፍ ቅዱስ የተያያዘ መገለጥ የሚናገር መሆኑን የሚከተለው አገላለጽ አጠቃላይ መጽሐፉን አያይዞ ለማየት ይረዳል ፡-
v ብሉይ ኪዳን የደሕንነት ማዘጋጃ
v ወንጌላት የደሕንነት ስራ
v የሐዋርያት ሥራ የደሕንነት አዋጅ
v መልእክቶች የደሕንነት ማብራሪያ
v ራዕይ የደሕንነት መደምደሚያ
መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የተሳሰረበትንና የተዛምደበትን ሁኔታ ስንጠብቅ ትርጉማችንን ትክክለኛ ለማድረግ የምንችልበትን አንድ መሰረታዊ የትርጉም መንገድ መከተላችን መሆኑ ማወቅ አለብን። አውድን ለመጥበቅ የምንከተላቸው መሰረታዊ የትርጉም ደንቦች የሚከተሉት ጠቃሚዎች ናቸው ፡-
- አንድ ጥቅስ ካለበት ክፍል ተገንጥሎ የብቻው ትርጉም እንዲኖረው ከተሳሰረበት ታሪክ ተለያይቶ መወሰድ የለበትም። !! ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት
የመወያያ ጥቅሶች ማቴዎስ 10፡9-10
ሲታይ አገልጋዮች ለመንገድ ምንም ነገር መያዝ እንደ ሌለባቸው መናገሩ ካለበት ክፍል ተገንጥሎ ከተወሰደ የተሳሳተ ትርጉም ያመጣል።
2. ግልጽ ያልሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ግልጽ በሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መፈታት አለበት
ለምሳሌ
Ø ኢሳይያስ 53 በአዲስ ኪዳን ግልጽ ፍቺ ያገኛል (የሐዋርያት ስራ 8፡26-35)
- የአውድ ሕግ በደንብ ከተጠበቀ የሚጠናውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተግባር ለማዋል የምንችልበትን መጠንና ሁኔታ ለመረዳት ትክክለኛ ግንዛቤ እናገኛለን።
መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እናጠናለን?
መጽሐፍ ቅዱስ ከማንኛውም መጽሐፍ በላይ በክብሮትና በጥንቃቄ መጠናት ያለበት መጽሐፍ ነው። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ያነቡታል እንጂ አያጠኑትም። ብዙ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት አላቸው ነገር ግን በውስጡ የተቀመጠውን ሐብት ቆፍረው ለማውጣት ግዜ አይሰጡትም። የወንጌል አማኞች ነን ከሚሉት መካከል 10%ያህሉ ብቻ በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ያነባሉ።
ከዚህ በታች መጽሐፍ ቅዱስ የሚነበብባቸው የተለያዩ መንገዶችና አይነቶች የሚከትሉት ናቸው፡-
- መፅሐፍ ቅዱስ የሚነበብ እንጂ የሚጠና አይደለም የሚሉ አንባብያን
- አልፎ አልፎ በገጠመኝ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ
- በፍቺ መጻሕፍት ብቻ በመደገፍ የሚያነቡ
- ላሉበት ሕይወት የሚረባ ነገር ብቻ ለማግኘት የሚያነቡ
- ተአምራዊ የሆነ አነባበብ የሚጠቀሙ
- በብልሃት ትክክለኛ የአጠናን ዘዴ በመጠቀም የሚያነቡ
አማኞች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ለምን ያጠናሉ?
v ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን እንዲድኑ ዮሐ.20፥30-31
v ራሳቸውን ማወቅ እንዲችሉ ያዕ.1፥22-25
v እምነት እንዲሆንላቸው ሮሜ 10፥14-16
v በፈተና ጊዜ ሐይል ለማግኘት መዝ.119፥11
v ምሪት ለማግኘት መዝ.119፥105
v ለበጎ ስራ ለመዘጋጀት 2ጢሞ.3፥16-17
v መንገዳችን እንዲቀናና የጌታ ሃሳብ በሕይወታችን እንዲፈጸም ኢያሱ 1፥7,8
v ለመንፈሳዊ ውጊያ የጦር እቃ እንዲሆንላቸው ኤፌ. 6፡17
የመፅሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ
መግቢያ ፡-
የሐኪሞች ፈተና
የአሳ ተማሪ
የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ
ዘርዘር ባለ መልኩ ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በተለያዩ መጻሐፍት ላይ የሚጠቆሙ ከአስራ ሁለት የማያንሱ የማጥኛ ዘዴዎች ይኖራሉ። አብዛኛዎቹ የጥናት ዘዴዎች ለግል ጥናት የሚመቹ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ለግሩፕ ጥናት ሊሆኑ የሚቹበት ሁኔታ ያታይል። ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው ፡-
1) የጥሞና ጥናት ዘዴ
በአንድ ጥቅስ ላይ መንፈስ ቅዱስ የመረዳትና የመገለጥ ጸጋ እንዲሰጥ በመጓጓት የሚደረግ የአጠናን ዘዴ ነው። ይህ ዘዴ ጌታ በተለያየ መንገድ በአንድ የመፅሀፍ ቅዱስ ክፍል ሲናገረን ያንን ክፍል በሚገባ ከሕይወት ጋር ለማዋሃድ ብለን በጸሎት መንፈስ ሆነን የምናደርገው ጥናት በዚህ ጥናት መሰረት የሚደረግ ጥናት ነው። ይህ በግል የጥሞና ግዜ ብቻ የሚደረግ ሲሆን ከቅዱሳን ጋር ሕብረት ስናደርግ የተማርነውን ለማካፈል የሚረዳንን ጸጋ የማናገኝበት መንገድ ነው።
2) የምዕራፍ ጥናት
ይህ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅስ በመደጋገም ካነበቡ በኋላ የምዕራፉን ማዕከላዊ ክፍል ጨምቆ ለማግኘት የሚደረግ ጥናት ነው። በዚህ ሁኔታ የተገኘውን የተጨመቀ ሃሳብ አሳጥሮ በመጻፍ የሚቻልበት ሁኔታ ይገኛል። ይህ አይነቱ ጥናት በመጽሀፍ ቅዱስ ጥናት ሊደረግ የሚችል ጥናት ነው።
3) የርዕስ ጥናት
ይህ ጥናት ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ጥናት ጋር የሚመሳስለበት ሁኔታ አለው። ለይት ባለ መልክ የሚጠናበት ባሕርዩ የሚጠናው ርዕስ ሰፊና የተለያዩ ጉዳዮችን የሚነካካ ሊሆን በመቻሉ ነው። ስለ ደህነት ቢጠና በቃል ጥናት ለየብቻቸው ሊጠኑ የሚችሉትን ሐጢያትን ፤ ምሕረትን ፤ ፍርድን ፤ ጸጋንና የተለያዩ ቃላቶችን ሁሉ ባካተተ መልክ የሚጠና በመሆኑ ሰፊና ግዜ የሚጠይቅ ነው። ጥናቱ በሚካሄድበት ርዕስ ላይ የሚናገሩ ጥቅሶችን በማስተያትና በማወዳደር ጥናቱ ስለሚካሄድ ጥቅሶቹን ከያሉበት ፈልጎ ለማግኘት የሚረዳ አጋዥ ማጥና መጽሐፍ አስፈላጊ ነው። በዚህ አይነት መንገድ የተገኘውን ጥናት አቀናጅቶና አጣጥሞ መልክ ባለው ሁኔታ ቢዘጋጅ ለሌሎች ትምሕርት ሆኖ የሚቀርብ መሆን ይችላል። ይህ አይነቱ ጥናት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ብዙ የተመቸ አይሆንም።
4) የባሕርያት ጥናት
የባሕርይ ጥናት የሚለው ከገፀ ባሕርያት ጥናት ይለያል። ይህ አይነቱ የአጠናን ዘዴ በአንድ መንፈሳዊ ባሕርይ ላይ የጌታ ቃል ምን እንደሚል ለማወቅ የሚደረግ ጥናት ነው። ይህ አይነቱ ጥናት የሚካሄደው የሚጥናውን ባሕርይ በግል ሕይወት ለማዳበር ወይንም አፍራሽ ባሕርይ ከሆነ ለማስወገድ የሚረዳ ጥናት ነው።
5) የመሪ ሀሳብ ጥናት
በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ሊጥና የሚችል በጣም ጠቃሚ የሆነ ጥናት ነው። በአንድ መንፈሳዊ ጉዳይ ላይ የጌታ ቃል ምን እንደሚል ለማወቅ የሚደረግ ጥናት ነው። በዚህ ጥናት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ አግባብ የሆኑ ትክክለኛ ጥይቅቄዎችን በመጠየቅ መጽሐፍ ቅዱስ መልስ እንዲሰጠን የምናደርግበት ጥናት ነው። ይህ አይነቱ ጥናት መጽሐፍ ቅዱስ በሚጠየቁት ጥያቄዎች ላይ ምን እንደሚል ለመመለስ መጽሀፍ ቅዱሳቸውን ከሚያውቁ ጋር ወንም በግል ሊደረግ የሚቀል ጥናት ነው።
6) የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ታሪክ ጥናት
በጌታ ቃል ታሪካቸው የተጠቀሱ ሰዎችን ታሪክ በማጥናት በሕይወታቸው ያለፈውን የጌታን አሰራርና ፈቃዱም በሐይወታቸው የተከናወነበትን ሁኔታ በማጥናት ራሳችንን የምናንጽበት የጥናት አይነት ነው። ይህ አይነቱ ጥናት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ሊጥና የሚችል በጥማ ጠቃሚ የሆነ ጥናት ነው።
7) የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ጥናት
በመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ስፍራ የያዙ ብቃላት ደረጃ ብቻ የሚጠኑ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ቃላቶች አሉ። ለምሳሌ እግዚአብሄር የሚለውን የመለኮት መጠሪያ ብቻ በመውሰድ በጣም ሰፊና ጥልቅ የሆነ ግዜ ሰፊ ግዜ የሚጠይቅ ጥናት ማድረግ ይቻላል። በዚሁ መልክ ፍቅርን ፤ ጸጋን ፤ እምነትን ፤ ሐጢያትን ፤ እምነትንና የመሳሰሉትን ሁሉ በቃላት ጥናት ማጥናት ይቻላል። ይህን የመሰለ ጥንት ለማጥናት የተለዩ የመጽሐፍ ቅዱስ አይነቶች ያስፈልጋሉ። ጦፒቻልየመዘገበ ቃላት ጥናት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ሁነኛ ቃላቶች ሊኖራቸው የሚችላቸውን ትርጉም በምንና በይት ሁኔታ ላይ እንድተጠቀሱ ለማወቅ የሚረዳ የአጠናን ዘዴ ነው።
ይህን አይነቱን ጥናት ለማጥናት የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስና የእንግዝሊዝኛም ሆነ የአማርኛ መዝገበ ቃላት መጻሕፍት ያስፈልጋሉ።
8) የመጽሐፍ ታሪካዊ ባሕላዊና መልክአ ምድር ጥናት
በዚህ ጥናት በሚነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ የተጠቀሰውን ታሪክ የሚመለከቱ የፖለቲካ የመልክዓ ምድር ሁኔታና የባህሉን ጉዳይ ለማጥናት የሚደረግ ጥናት ነው። ይህ አይነቱ ጥናት ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ የሚነበቡ መጻሕፍት ሳይኖሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ተመስርቶ ሊደረግ የማይችል ጥናት ነው። የዚህ ጥናት አለማ መጽሐፍ ቅዱስን በተጻፈበት ዘመን ሁኔታ በማጥናት ትክክለኛ መረዳት ለማግኘት የሚደረግ ጥናት ነው።
9) የአንድ መጽሀፍ አሰሳ ጥናት
ይህ አይነቱ ጥናት አንድን የመጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ መጽሐፍ የሚመለከት ጥናት ነው። የሚጠናውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ደጋግሞ በማንበብ አጠቃላ መልእክቱ ምን እንደሆነ ለመረዳት ሙሉ መልእክቱን ለማግኘት የሚደረግ ጥናት ነው።
10) የምዕራፍ ትንተና ጥናት
ይህ አይነቱ ጥናት የሚካሄደው የመጽሐፉ ምዕራፍ የት ቦታ ላይ እንድተከፍለ በትክክል የታወቀ ከሆነ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ የምእራፎችና የጥቅሶች አከፋፈል ሁልግዜ ትክክል አይደለም። ሃሳቦች ተገንጥለው በምዕራፍ ተለያይተው ካጠናናቸው ትክክል የሆነ ግንዛቤ ላናገኝ እንችላለን። ከዚህ የተነሳ አንድ ሙሉ ሃሳብ የሚጀምርበትን የምዕራፉን ታሪክ ክፍል ቀደም ካለው ምዕራፍ የምናገኝ ከሆነ ያንን ሁኔታ እግምት ውስጥ ማስገባት አለብን። የምዕራፍ የትንተና ጥናት ሙሉ እንዲሆን የተለያዩ የአጠናን ዘዴዎችን በመጠወም ጥናቱን ውጤታማ ማድረግ ይችላል።
11) የአንድ መጽሐፍ የትንተና ጥናት
ይህ አይነቱ ጥናት ከአሰሳ ጥናት የሚለየው መጽሐፉ ተደጋግሞ ከተነበበ በኋላ በውስጡ የያዛቸውን መሰረታዊ መልእክቶች ልማግኘት በሚያስችል ግንዛቤ መጠናቱ ነው። የመጽሐፉን መሪ ሃስቦችና መሰረታዊ መልእኽቶች ምን እንደሆኑ ለመረዳት በሚደረገው ጥናት መጽሐፉን ደረጃ በደረጃ በሃስብ እየከፋፈሉ ማጥናት ይጠይቃል።
ይህ ጥናት የሚፈለገው ውጤት እንዲገኝበት ከተፈለገ ቀደም ብሎ
i. የመጽሐፍ አሰሳ ጥናት
ii. የመጽሐፉ የምዕራፎች ትንተና ጥናት
iii. በመጨረሻም የአጠቃላይ የመጽሐፍ ትንተና ጥናት በማስከተል ውጤታም እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።
ይህንን ጥናት ስናጠና ከላይ ከጠቀስናቸው የአጠናን ዘዴዎች መካከል አንዳንዱ በአጋዥነት ለዚህ ጥናት የሚረዳ ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ከዚህ የተነሳ የቃላት ፍቺ ጥናትን ከታሪክና የባሕል እንዲሁም የመልከ ምድሩን ጀርባና የጸሐፊውን እንዲሁም የተጻፈላቸውን ሰዎች ሁኔታ ለማጥናት የሚገባ ይሆናል።
12) ጥቅስ በጥቅስ የሆነ የትንተና ጥናት
ይህ ጥናት ከላይ ያየናቸውን ጥናቶች በተጣራ ሁኔታና በጥልቀት ዝርዝር መልካቸውን ለማጥናት ጥቅሶችን ከጥቅሶች በማገናዘብ ከመልእኽቱ ጋር በመቀራረብ ሙሉ ሃሳቡን ለማግኘት የሚረዳ አጠናን ዘዴ ነው።
ይህ ጥናት ሲጠና ጥቅሶቹን ተመሳሳይነት ካላቸው ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር በማስተያየት ለማጥናት አስፈላጊ ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ይህንን ለማድረግ ተመሳሳይ ጥቅሶን የሚያያይዙ መጽሐፍ ቅዱሶች (ክሮስ ሪፈረንስ ባይብል) በግድ አስፈላጊ ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም የጥቅሶቹን መልእክት በትክክል ለመረዳት እንዲቻል ሌሎች ትርጉሞችን መመልከት ይኖርብናል።
በዚህ ስልጠና የሚተኮርበት የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ ከዚህ በታች ከተጠቀሱት መካከል የመጀምሪያው ሰፊ ገለጻና ማብራሪያ የተሰጠበት አጠናን ዘዴ ነው።
- የኢንዳክቲቭ የአጠናን ዘዴ
Ø በኢንዳክቲቭ አጠናን ዘዴ ስለ አንድ ነገር ምንነት ከመወሰን በፊት ለውሳኔ የሚያበቃ ማስረጃ ለማግኘት ምርመራ የሚደረግበት የአጠናን ዘዴ ነው።
Ø ኢንዳክቲቭ እንደ ንብ ማር ለመስራት የሚያስችላትን የአበባ ቅመም ለመሰብሰብ የአበባዉን አይነትና ሁኔታ እያጤነች ለማር ስራ የሚሆነውን እንደምትሰበስብ አይነት ነው።
Ø ኢንዳክቲቭ ማስረጃን የመመርመር ተግባር ነው።
Ø በኢንዳክቲቭ አጠናን በባሕርዩ የሚጠናውን ነገር አስመልክቶ ነቂስ በነቂስ ምኑም ሳይቀር እንዳለ የሚጠናበት ዘዴ ነው
- ዲዳክቲቭ የአጠናን ዘዴ
Ø በዲዳክቲቭ የአጠናን ዘዴ አቋም በተወሰደበት ጉዳይ ወይንም ሃሳብ ላይ ድጋፍና ማስረጃ ለማግኘት የሚደረግ የአጠናን ዘዴ ነው።
Ø ዲዳክቲቭ አንድ ግምታዊ ሃሳብን በመያዝ ያንን ህሳብ የሚደግፍ ማስረጃ ለማቅረብ የሚረዳ የአጠናን ዘዴ ነው ።
Ø ዲዳክቲቭ ማስረጃ ማግኘት ላይ ያተኩራል። በአንድ በተወሰደ ሃሳብ ላይ ዲዳክቲቭ ማስረጃ የማግኘት ዘዴ ነው።
a. የዲዳክቲቭ አጠናን ዘዴ ጥቅም
i. መጽሐፍ ቅዱስን የእግዚአብሔር መገለጥ አድርጎ ይቆጥራል
ii. የአምላክ መገለጥ የሆነውን ቃል ደረጃ
b. የዲዳክቲቭ አጠናን ዘዴ ያለው ጉድለት
i. በሰው አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ድምዳሜ ላይ የመውደቅ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።
ii. መጽሐፍ ቅዱስን በስርዓት ተርጉሞ ወደ እውነት ከመድረስ ይልቅ ቅኖናዊ (ዶግማቲክ) አቃም የማበጀት ዝንባሌ ያስከትላል።
iii. ሰው በመገለጥ ካልሆን በስተቀር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ወደ እውነት መድረስ አይችልም የሚል ድምዳሜ ሊያስከትል ይችላል።
ሁለቱም የጥናት አይነቶች ይደጋገፋሉ
ንቧ ቀፎ ሳይኖራት አበባ እንደማትቀስም ሁሉ የሚያጠናበት አላማ ሳይኖረው መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠና ሰው ዓላማ የሌለው ጥናት ያጠናል።
ሸረሪቷም የያዘቸውን ምንነት ስታጤንና ሳትመለከት እንደማትበላው ሁሉ በዲዳክቲቭ ዘዴ የተገኘው ማስረጃ ምንነት ሳይታይ ለማስረጃነትም ሆነ በተግባር የሚተረጎም አይሆንም
በግሩፕ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ምቹ የሆነው ዘዴ የኢንዳክቲቭ የአጠናን ዘዴ ነው። ይህ ዘዴ የጥናቱ ተሳታፊዎች በሚያጠኑት ነገር ላይ የራሳቸው የሆነ የግል ግንዛቤና መረዳት እንዲኖራቸው የሚርዳ አጠናን ነው።
የኢንዳክቲቭ አጠናን ለግሩፕ ጥናት ብቻ ሳይሆን በግል መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትም የሚረዳ አጠናን ነው።
በኢንዳክቲቭ ዘዴ መጽሀፍ ቅዱስ ሲጠና የምንመለከታቸው አራት አይነት ዓይነት የአጠናን ሂደቶች ይኖሩታል፡-
1. መመልክት (ኦብዘርቬሽን)
2. መተርጎም (ኢንተርፕርቴሽን)
3. ማገናዘብ (ኮር-ሪሌሽን)
4. በተግባር ማዋል (አፕልኬሽን)
መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ከመጀመራችን በፊት ከመጽሐፉ ጸሐፊ ጋር ለመገናኘት ራሳችንን ማዘጋጀት ይገባናል።
በጸሎት ጀምር
በዮሐንስ ወንጌል ም 16፡3-15 ስንመለከት ወደ እውነት የሚመራን መንፈስ ቅዱስ እንደ ሆነ ያስተምረናል። የእግዚኣብሔርን እውነት ወስዶ ለእኛ የሚገልጠው እርሱ ብቻ ነው።
የእርሱ መገኘትና ተሳታፊነት ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል። '' የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው'' አለ ጌታ ኢየሱስ ( ሉቃስ 4፡19 )። እርሱ ብርሃን ላልሆነልን የቃሉን ብርሃን ማየት አንችልም። መንፈስ ቅዱስ በፕሮግራም መክፈቻ ፀሎት መጋበዝ ላይ ሳይሆን ትልቁ ቁም ነገር መኖሩን አውቆ በመረዳትና በማስተዋል በተሞላ ልብና ትህትና አስተማሪ የሆነውን እርሱን ማየትና መመልከት ነው። ጥናታችን ስïጀመር እስክምጨረሻው በፀሎት መንፈስ ሊያቆየን በሚያስችለን ጸሎት መጀመር አለበት።
የሚጠናውን ክፍል መለየት
የሚጠናውን ክፍል መለየት አለበት። የምናየውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያለበትን ሁኔታ የመልእክቱን አካባቢ፣የተመሰረተበትን ይዘት መረዳት አለብን። የክፍሉ አካባቢ አውድ ዳርና ድንበሩን መለየት አለብን። የምናጠናው ክፍል አለቦታው በመዕራፍ የተቆረጠ ጥቅስ ወይንም አንቀጽ እንዳይሆን ሃሳቡ በትክክል ከየት ጀመሮ የት እንደሚያልቅ መለየት ይገባናል።
አውድ አንድ እንቂራሪት የምትኖርበትን ኩሬ ይመስላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ካለበት ትክክለኛ ቦታው ሲወጣና ያለቦታው ሆኖ ሲታይ የተሳሳተ እይታን ያመጣል።
የብሉይ ኪዳን በጥቅሶች የተከፈለው ከጥንት ጀምሮ እንደ ሆነ መጻሕፍት ይናገራሉ። በብሉይ ኪዳን ያለው እያንዳንዱ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ከእንግሊዝኛው ካፒታል ሌተር "T" ጋር በሚመሳሰል አጠር ባለ የቅርጽ ምልክት ጥቅሶቹ ተከፋፍለው እንደሚገኙ ይነገራል። አይሁዳውያኑ ይህንን ምልክት "ሲሉክ" በማለት ይጠሩታል።
በአዲስ ኪዳን ጻህፍት የምንላቸው በጥንት ዘመን የሚጠሩት "ሶፈሪም" ተብለው ነበር። ትርጉሙ "ቆጣሪዎች" ማለት ነው። በዚህ ስም የተጠሩበት ትልቁ ምክንያት መጻሕፍትን በኣቸው ከገለበጡ በኋላ የተገለበጠው መጻሕፍ ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ እያንዳንዱ ቃል ተቆጥሮ ትክክለኛ ቁጥር ማሳየት ነበረበት። ከዚህ የተነሳ ከጸሐፊነታቸው ይልቅ የገለበጡትን መጽሐፍ ትክክለኛነት በሚያሳይ የቆጠራ ስራቸው ይጠሩ ነበር። በጥንት ማሶራ እንደሚታይው 23,203 ቃላት ይቆጠሩ እንደነበር ይነገራል።
የምዕራፍና የጥቅስ ክፍፍል ታሪክ
የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በየመጽሐፉ ጠርዝ ላይ የአሃሳብ አንድነት ያላቸውን ጽሁፎች በአንድ መደብ ለመክፈል በሚጠቅም ምልክት ተከፍለው እንደነበር ይነገራል። በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ታሪያን የተባለ ሰው ወንጌላትን "ከፋሊያ" በሚል ወይንም ርዕስ በሚል አከፋፈል ከፍሎአቸው እንደነበር ይነገራል።
በሶስተኛው ክፍለ ዘመን አሞኒየስ የተባል ሰው መጽሐፍትን በስሙ መጠሪያ ባወጣላቸው ክፍሎች ክፍሎአቸው እንደነበር ይነገራል። በአምስተኛው ክፍለ ዘመን የአለክሳንድርያ ዲያቆን የነበረው ዩታሊየስ የጳውሎስን ፤ መልእክቶች ግብረ ሐዋርያትንና ሌሎችንም መጻሕፍት በሙሉ ቲታንየስ በወንጌሎች እንዳደረገው ከፍሎአቸው ነበር።
ይንን ክፍፍል በራዕይ መጽሐፍ ላይ በሃያ አራት አንቀጾች በመክፈል እንድርያስ የተባለው የቂሳሪያ ጳጳስ የአዲስ ኪዳንን ክፍፍል አጠናቀቀ። ታሪኩ እንደሚያሳየው ይህ በግለሰቦች ጥረት የተደረገው አከፋፈል መንፈሳዊ ምስጢር የሌለው በመሆኑ ለስህተት የተጋለጠ አከፋፈል ነው።
ዛሬ በብሉይና በአዲስ ኪዳን ላይ የምናየው የምዕራፎችና የጥቅሶስ መከፋፈል ሙሉ በሙሉ ተከፍሎ የታየው ስቴቨን ላንግተን በተባለ የካንተር ቤሪ ቢሾፕ ነው። ይህ ሰው የላቲኑን ቩልጌት 1228 በምዕራፎች ከፋፈለ። ከዚያም 1248 ሁጎ የተባለው ሰው የላንገተንን የምዕራፍ ክፍፍል ለመጨመር በፊደላት አድርጎ ምዕራፎቹን እንደ ከፍለ ይነገርለታል።
የፊደላት አከፋፈሉ በቂና የሚመች ሆኖ ባለመገኘቱ 1551 ሮበርት እስጢፋኖስ የተባለው ሰው በጄኒቫው ትርጉም ላይ በቁጥር ጥቅሶችን እንደለየ ይነገርለታል። 1560 ለመጀመሪያ ግዜ በጄኔቫው ትርጉም ላይ እያንዳንዱ ጥቅስ እንደ አንድ አንቀጽ በመወሰድ በተግባር ላይ ዋለ።
ከዚያም ወዲህ በ1611 ላይ በኪንግ ጀምስ ትርጉም ላይ ይህ ክፍፍል በስራ ላይ ዋለ። ይህ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ የዋለው ክፍፍል ለመጀምሪያ ግዜ በብሉይ ኪዳን ላይ የዋለው በ1338 በመምሕር ሰሎሞን ቤን እስማኤል እንደ ነበር ይነገራል። እኝህ አይሁዳዊ መምህር ክርስቲያኖች በየተጠቀሙበትን አከፋፈል በመውሰድ አመቺ ሆኖ እንዲገኝ በማለት በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ላይ አውለውታል።
የምዕራፍ አከፋፈሉ የሚያሳየው ጉድለት
1. 2ኛ ነገስት ምዕራፍ 6 እና ምዕራፍ 7 መከፍል በሚገባቸው ቦታ ላይ አልተክፈሉም። በMኦራፍ 7 ላይ የተመደቡት ቁጥር 1 እና 2 በምዕራፍ 6 ላይ ቁጥር 33 እና 34 ሆነው መመደብ ነበረባቸው።
2. ኢሳይያስ 8 እና 9 ለሁለት መከፈል አይገባቸውም ነበር።
3. ኢሳይያስ 52፡1-12 የኢሳይያስ 51 ክፍል ሆኖ ማለ ሲገባው በኢሳይያስ 53 ላይ ከቁጥር 11-15 ላይ ከሚገኘው ሃሳብ ጋር በማያያዝ ሃሳቡን ገነጣጥሎ መድቦታል።
4. በዲስ ኪዳን በማቴዎስ 9፡35-38 ላይ ከምዕራፍ 10 ጋር የሚሄድ መንፈስ አለው።
5. ብዮሐንስ 8፡1 ላይ የተጠቀሰው የዮሐንስ 7፡54ኛ ቁጥር መዝጊይዝ ሆኖ መቅረብ ነበረበት። ሰው ሁሉ ወደ ቤቱ ሲገኣ ጌታ ወደ ደብረ ዘይት መሄዱ ተነጻጽሮ ተጽፎአል።
6. በሐዋርያት ስራ ላይ 4፡36-37 የተጠቀሰው የምዕራፍ 5 መጀመሪያ መሆኑ መልካም ነበር።
7. የሐዋርያት ስራ ምዕራፍ 6 እና 7 አጉል ቦታ ላይ ተለያይተዋል። ሊቀ ካህኑ "ይህ ነገር እንዲህ ነውን?" ብሎ የሚጠይቀው ጥያቄ ከላይ የሐሰት ምስክሮች ያቀረቡበትን ምስክርነት አስመልክቶ የሚጠይቀው ጥያቄ ነው። የእስጢፋኖስ ፊት የተለወጠው ከሳሾቹ ከተናገሩ በኋላ ሊቀ ካህኑ ከመጠየቁ በፊት ነበር። የሊቀ ካህኑ ጥያቄ ከከሳሾቹ ምስክርነት ጋር ተለይቶ በሌላ ምዕራፍ መሆን አልነበረበትም።
8. የሐዋርያት ስራ 8፡1 የተጀመረው በምዕራፍ ሰባት ያላለቀውን ሃሳብ ይዞ ነው።
9. እንዲሁም የሐዋርያት ስራ 22፡1 በጭራሽ መከፈል በማይገባው ስፍራ የምዕራፍ 21፡40 ቀጣይ ሃሳብ ይዞ ነው የተለየው። "እንዲህ አለ …" ብሎ ያለውን መቀጠል ሲገባው አዲስ ምዕራፍ በመክፈት የተባለውን ለብቻው ያደርጋል።
10. ሮሜ ምዕራፍ 4 ማለቅ የነበረበት በሮሜ 5፡11 ደርስ ያልወን ሃሳብ በስሩ በመያዝ እንደነበር የሃሳቡ መያያዝ ያንን ያመለክታል።
11. ሮሜ 6፡1 የተጀመረበትና ሮሜ 7፡7 የሚናገረው የሃሳብ መከፋፈልን ያልጠበቀ የምዕራፍ አከፋፈል እንዳለ ይታያል።
12. ሮሜ 15፡1-7 የሮሜ 14 ክፍል ሆኖ ማለቅ ይገባው ነበር። ሮሜ 15፡7 እና ከቁጥር 8 በኋላ ያሉት ሃሳቦች በአንቀጽም ሆነ በምዕራፍ አንድ አይነት ሃሳብን ይዘው አይወርዱም።
13. 1ኛ ቆሮ.11፡1 የ1ኛ ቆሮ. 10 መደምደሚያ መሆን ይገባው ነበር።
14. 2ኛ ቆሮ.6 ማለቅ የሚገባው በ2ኛ ቆሮ. 7፡1 ላይ ነበር። ስለ ቅድስና የሚናገረው የምዕራፍ 7፡1 ሃሳብ በስድስት ላይ ካለው ተገንጥሎ ለብቻ ነው ያለው። 7፡2 አዲስ ሃሳብ ይጀምራል። በ7፡1 ላይ "የዚህ ተስፋ ቃል ካለን" የሚለው አባባል በ6፡16-18 የተጠቀሱንት ተስፋዎች ተንተርሶ ነው የሚናገረው።
15. ፊልጵስዩስ 4፡1 ላይ ያለው ሃሳብ በፊልጵስዩስ 3 ላይ ማለቅ የነበረበት ሃሳብ ነው። 4፡2 ላይ ከቁጥር 1 ጋር ጨርሶ አይገናኝም። በ4፡1 ላይ ያለው "ስለዚህ" የሚለው አያያዥ ከምዕራፍ 3፡4 ሃሳብ ጋር መገንጠሉ ትክክል አይደለም።
(Context) ለቃላት፣ለሐረጎችና ለአረፍተ ነገር
አንድን ቃል፣ሐረግና አረፍተ ነገሮች የከበቡት ቃሎች፣ ሐረጎች ፣አረፍተ ነገሮች ናቸው። እነዚህ ሌላውን የከበቡት ቃሎች፣ሐረጎችና አረፍተ ነገሮች ጸሐፊው በዚያ ቃል ምን ለማለት እንደፈለገ መረዳት ይሰጡናል። እነዚህ የቃላት፣የሐረጎችና የአረፍተ ነገሮች ስብስቦች የመፅሃፍ ቅዱስን አውድ (Context) ይፈጥራሉ። ይህ ሁኔታ ለአንቀጽ ለምእራፍና ለመጽሃፍ ብሎም ለኪዳንና ለአጠቃል መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ የሚሆን አውድ እንደሚኖር ያሳያል።
(Context) አውዱ የአንድን ትርጉም ይዘት ስለሚወስን የአንድን ምንባብ አውድ በደንብ መመልከት ይገባል።
አንድ ቃል የተለየ ትርጉም የሚሰጥ ከሆነ በቃሉ ብቻ ተወስኖ ትርጉም ከመስጠት ቃሉ ባለበት ክፍል የአጠቃቀሙ ይዘት ምን መልክ እንዳለው መመልክት ተገቢ ነው።
በአንድ ምንባብ ውስጥ ቃሎች እንዴት እንደተያያዙን እንደተዛመዱ በማየት ቃሎቹ የሚሰጡት መልእክት ወይንም ሊይዙት የሚችሉት ትርጉም ምን እንደሆነ ለመለየት የሚያስችል ግንዛቤ በቀላሉ ይገኛል።
ጉልህ የሆነውን ክፍል ተመልከት
መመልከት ስትጀምር ጎልቶ የሚታየውን በማየት ጀምር።
ለምሳሌ - ስለ ሰዎች የተጻፍውን እውነት ፣ስለ ቦታዎች ፣ ወቅት ( ጊዜ)
ሰዎች ፣ ቦታና ጊዜ በቀላሉ የሚታዩ ናቸው። ዋና ዋናውን ላይ ስናተኩር ጎልተው የሚይያዙ ነገሮች ቶሎ ይታዩናል።
ለምሳሌ - የሚሰካኩ ስእሎችን ስንሰራ ከየት እንጀምራለን?
· ከአራቱ ማእዘን
· ቀጥ ያሉትን ጠርዞች
· ከዚያ ወደ መሃሉ እንገባለን
ልክ እንደዚïሁ ጎልቶ የሚታየውን አውራ እውነት ካየን መፅሃፉን ለማጥናት የሚያስችል መስመር (መንገድ) እንይዛለን።
በተጨባጭ መልኩ ማየት አለብን
ክፍሉ ለራሱ ይናገር። ክፍሉን በጥንቃቄ የምናየው የክፍሉን ይዘት (ሆተቦtቅኃt) ለማየት ብለን ነው፣ይህንንም የምናደርገው ክፍሉ የሚደጋግመውን ዋና ሃሳቡን ለማግኘት ነው።
የእግዜአብሔርን ቃል ስናጠና ለራሳችን አንድ ነገር ለማግኘት ባለ ፍላጎት ሳይሆን መቅረብ ያለብን እግዜብሔርን በራስé ፍላጎት ምን እያለ እንዳለ ለማወቅ ብለን ማጥናት ይኖርብናል። ለአንድ ለምንፈልገው መረጃ ለማግኘት ወይንም አንድን ሰው የሚናገርልንን እውነት ለመፈለግ ብለን ማንበብ የለብንም። የእግዜብሔርን ቃል የሰው መልእክተኛ ማድረግ ታላቅ በደል ነው።
እግዜአብሔር ቃሉን በመጠቀም የሚቀድስን እርስé እንድናውቀው የሚፈልገውን እውነት በማሳወቅ ነው። ዮሃ. 17፡17 '' ቃልህ እውነት ነው በቃልህ ቀድሳችው '' ስለሚል በቃሉ ለመቀደስ የቃሉን እውነት ማወቅ አለብን። የምንቀድሰው የእግዜአብሔርን ፈቃድና ሃሳብ ለይተን ለተረዳነው ቅደêስ ፈቃድ ለመገዛት ራሳችንን ስንሰጥ ነው።
በተጨባጭ የታየ አንድ የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍል የሚያስተላልፈው እውነት ምንጊዜም እውነት ሆኖ ይኖራል። የቱንም ያህል ጊዜ ቆይተን ብናየው ፣አንባቢዎች ቢለዋውጡም ያ እውነት ከአንባቢው ከራሱ የመጣ እስካልሆነ ድረስ በክፍሉ ያለ ከሆነ ለሌሎች አንባቢያንም ይታያል። ይህን በመሰለ በማይለወጥ እውነት ላይ ነው ህይወታችን መገንባት ያለበት። ስለዚህ በተጨባጭ መፅሃፍ ቅዱስን እናጥናው። የራሳችን አስተያየትና አመለካከት ሳንጨምር ለማጥናት እምነት ከመስማት መሆኑን በመረዳት የቃሉን ባለቤት እንዳወቁ ሰዎች በመንቀጥቀጥና በፍርሃት ለመማር መዘጋጅት ይኖርብናል።
እግዘአብሔርን ቃሉን ብቻ በመላክ የፈጠረና የፈወሰ አምላክ ስለሆነ ከመልእክተኛው ቃሉ ጋር በማገናኘት የአምላካችን ተምራት በሕይወታችን ይፈፀም። ይህ ሚስጥር የገባው ንጉስ ዳዊት '' አይኔን ክፈት ከሕግም ተአምራትን አያለሁ።'' ያለው እኔ ተመልካች ልሁን ፣ ወደ ቃልህ ስመጣ የሚያስፈልገኝ አይን ነው የሚል ይመስላል መዝ (115፣18)። ቃሉ ለራሱ ያገለግልሃል። ህያው ቃሉን ልኮ የፈወሰው ጌታ ለኛም በዚያው ቃሉ ያገለግለናል። ይህ እንዲሆን ግን ክፍሉን ለማግኘት እንድንችል ምንባቡን በተጨባጭ እንየው። የሚደጋገመውን ሃሳብ ተመልከተው። በዚሁ ሁኔታ ቃሉን በማጥናት ለራስህ በማዋል በተግባር ልትተረጉም ብትነሳ አስተማማኝ መሰረት ላይ ትሆናለህ።
መፅሃፍ ቅዱስ በተጨባጭ ማጥናጥ እንደሚገባ ሁሉ ቃሉ የሚንገርህን እውነት በግል ሕይወትህ ለማዋል መለስ ብለህ በአድናቆት እይታ የቃሉ ነፀህራቅ በራስህ ልብ ላይ ውሎ በአይነ ህሊንህ ተመልከተው። በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ቃሉን በመጠቀም በልብህ የቃሉን የህያውነት ስራ ይሰራልሃል። በዚህ ጊዜ ነው እግዜአብሔር ለአንተ መልእክት እንዳለው በግልህ እንደተናገረህ የምታውቀው።
ስለዚህ በ(ኢንዳክቲቭ) አጠናን መፅሃፍ ቅዱስን ስታጠና በአምልኮ፣ በመሰጠትና በጥሞና መንፈስ አጥናው። እግዚአብሔር በቃሉ የሚገለጥ አምላክ ነው። መንፈስ ቅዱስን የሚገልጠው የሰጋው ስራ በቃሉ ገበታ ፊት ብትሕትና መንፈስ ሆነው ለሚቀመጡ ይሰጣል። እግዚአብሔር ምን ይለኛል በሚል በሚያጓጓና በተጠማ ልብና ከጌታም ለመስማት በናፈቀ መንፈስ ተዘጋጅተህ አንብበው። እግዚአብሔር በቃሉ ለግልህ ይናገርሃል። እያጠናህ ሳለህ እግዚአብሔርን ለመስማት ጊዘ ውስድ።
የሚለውን ለማወቅ የሚጓጓ ሰው ሆንህ ጥያቄ እየጠየቅህ አንብበው
መፅሃፍ ቅደêስን በአላማ ለማጥናት ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልጋል። ክፍሉን እንደ አንድ መርምሪ ፖሊስ ጥያቄ ጠይቀው። ሊዘግቡት የሚገባውን ሙሉ ታሪክ ለማወቅ ጋዜጠኞች 5W እና 1H የሚባሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ማራሉ።
v Who? ማን ?
v What? ምን ?
v When? መቼ ?
v Where? የት ?
v Why? ለምን ?
v How? እንዴት?
እኛም የጥናት አላማችን ግቡን እንዲመታ እነዚህን ጥያቄዎች እንጠይቃለን።
1. ማን? ማን ፃፈ ፣ማን አለ ? ዋና ዋናዎቹን ገፀ ባሕርያት እነማን ናችው? ፀሃፊው ለማን ይናገራል? የተነሱት ሰዎች እነማን ናቸው? ስለ ማን ያወራል?
2. ምን? ዋና ዋናዎቹ ሁኔታዎች ምንድር ናቸው? ዋና ዋናዎቹ ህሳቦች ምንድርናቸው። ዋናው ትምህርት ምንድርነው? ሰዎቹ ምን ይመስላሉ? አብዝቶ ስለምን ይናገራል? ይህንን በማለት ሊያስተላልፈው የወደደው ምንድርንው?
3. መቼ? መቼ ተጻፈ? ይህ ታረክ መቼ ሆነ ? መቼ ይሆናል? መቼ አለ? መቼ አደረገ?
4. የት? የት ተደረገ? ይህንን ያለው የተ ነበር? የት ይሆናል?
5. ለምን? ይህንን ለመጻፍ ለምን አስፈለገ? ለምን ተወሳ? ለዚህ ሁኔታ ለምን ጥቂት ስፍራ ብቻ ተስጠው? ይህ ጉዳይ ለምን ተጠቀስ? ይህንና ያንን ለምን አደረጉ?
6. እንዴት ? እንዴት ተደረገ? እንዴት ሆነ? ይህ እውነት እንዴት ተገለጸ?
በዚህ ሁኔታ ጥያቄ የምናቀርበው ለምንባቡ ለራሱ እንጂ ለራሳችን ወይም ለአድማጭ አይደለም። ክፍሉ ለተጠየቀው መልስ ስïሰጥ ያስደንቃል።
እነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛ የሆነ የመመልከት ይዘትን የሚሰሩ ነጥቦች ናቸው። ለትክክለኛ ትርጉም የሚረዳውን መሰረት የሆነውን መመልከትን ይገናባሉ።
መመልከት በግባቡ ሳይመሰረት ወድር ትርጉም ከተሮጠ የሚከተለው የራሳችንን አስተሳስብና አመለካከት መናገርን ይሆናል። ሌሎች ያሉት እኛ የምንሰጥጠወን ወይም የተሰማንን ስንናገር ልክ አይመጣም። በዚህ መንገድ የምንጓዝ ከሆንን መፅሐፍ ቅደêስን እናጣምማለን።መፅሐፍትን ለገዛ ራሳችን ልንተረጉም ያልተፈቀደውን በማድረግ ጥፋትን እናመጣለን።
ለምሳሌ ማቴ 9፣18-25 ማን ታመመ? ማን ለመነ? ማንን እናያለን? መቼ ይህ ሁኔታ ሆነ? ምን አለ? እንዴት ለመነ?
እነዚህ 5ሬ እና1ሓ ጥያቄዎች ሁልጊዜ መጠየቅ አለባቸው ማለት አይደለም። ደግሞም በተጠየቀ ቁጥርም መልስ ይገኝላቸዋል ማለት አይደለም።
የመፅሐፉን አጠቃላይ ይዘት ማወቅ
የመፅሐፉን ስነፅሁፋዊ ባሕርይ ለይ
- ታሪካዊ ኢያሱ
- ወንጌል ማቴዎስ፣ ማርቆስ ወዘተ
- ቅኔና ግጥም መሐልይ፣መዘሙረ ዳዊት
- ምሳሌ መጽሐፈ ምሳሌ
- ትንቢት ኢሳያስ፣ ኤርምያስ ወዘተ
- ደብዳቤ የጳውሎስ መልእክቶች
- ሁለት መልክ ያለው ዳንኤል
የመፅሐፉን ታሪካዊ ገፅታ ለማየት የሚረዱ ጥያቄዎች
1. ለማን ተጻፈ? ስለ ራሱ ምን ይላል?
2. ያለበት ሁኔታ ምንድርነው? የት ነው ያለው?
3. ባለበት ቦታ ምን ሊያደርግ ነው ያለው?
4. በየትኛው እድሜ ላይ ነው የጻፈው?
የመፅሐፉን አላማ ለማወቅ የሚጠየቁ ጥያቄዎች
1. ለምን ይፅፋል?
2. ይህንን ለምን ያደርጋሉ?
3. እንዲህ ባለ መንገድ ለምን ይናገራል?
የመፅሐፉን መሪ ሃሳብ ለማግኘት የሚጠየቁ
- ፀህፊው አብዝቶ ለምን ይናገራል?
- ሰዎቹ ምን እንዲያደርጉ/እንዳያደርጉ ይፈልጋል?
ዋና ዋና ክንዋኔዎችን (ድርጊቶችን) ለይ
ለምሳሌ ፡-
1. ዘፍጥረት ምዕ. 1-11 ቢጠና
i. ምዕ. 1 እግዜአብሔር አለምን መፍጠሩ
ii. ምዕ. 3 የሰው ውድቀት
iii. ምዕ. 6-11 በኖሕ ዘመን የውሃ ጥፋት
2. ዘፍጥረት ምዕ. 12-50 ቢጠና
v በአብርሃም፣በይስሃቅ፣በያዕቆብና በዮሴፍ ሕይወት ላይ ያተኮረ እንደሆነ
እንመለከታለን።
የምንባቡ ቁልፍ የሆኑ ቃላቶችን ሐረጎችና አረፍተ ነገሮችን ልብ በል
ሀ) ቁልፍ ቃላት እንደ ቁልፍ መልእክቱን ይከፍታሉ።
መልእክቱን ለመረዳት ዋና የሆኑ ቃሎች ናቸው።
እነዚህ ቃላት ስሞች ፣ ቅጽል ወይንም ግሶች ሊሆኑ ይችላሉ
1. ቅፅሎች ገላጭ ቃላት ናቸው።
2. ግሶች ድርጊት ገላጭ ናቸው።
ቁልፍ ቃላትን ከክፍሉ ካወጣን ምንባቡ ትርጉም የለሽ ይሆናል።
ቁልፍ ቃላትን በመደጋገም ፀሃፊው ሃሳቡን ለማፅናትና ለማስጨበጥ ይጠቀምባቸዋል።
ድግግሞሹ በመፅሃፉ ምእራፎች፣ ወይንም በተወሰኑ አንቀጾች ሊሆኑ ይችላሉ።
ለምሳሌ ፡ 1) በ1ኛ ዮሐ. ላይ የሚከተሉትን ቃላት ተደጋግመው እንመለከታለን።
ፍቅር፣ሐጤአት፣መኖር፣ማወቅና ህብረት
2) 1ኛ ጢሞ. ሲጠና የሚከተሉት ቃላት ተደጋግመው
እንያለን። ሰንሰለቴ፣መከራ፣ስደቴ
ቁልፍ ሐረጎችና አረፍተ ነገሮች
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በመፅሐፈ መሳፍንት ላይ በተደጋጋሚ '' የእስራኤልም ልጆች በእግዜብሔር ፊት ክፉ የሆነ ነገር አደረጉ'' የሚል አረፍተ ነገር በተደጋጋሚ እናያለን። ይህ አጠቃላይ ሃሳብ የመፅሃፉን ቅንጅት በምን ላይ እንዳተኮረ እንድናይ ይረዳናል።
እያንዳንደê ቁልፍ ቃልና ሐረግ ማን ነው? ምንድነው? መቸ ነው? የት ነው? ለምንድነው? እንዴት ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ይረዳናል።
መሪ ሐሳብ
የምንባቡ መሪ ሃሳብ ለመረዳት በቃላት ድግግሞሽ በተለያየ ሁኔታ የሚገልጸውን ሃሳብ ማየት ያስፈልጋል።
§ ቁልፍ ቃል ሃሳቦችን ይገልጻለል
§ ሃሳብ መሪ ሃሳቦችን ይገልጻል
§ መሪ ሃሳብ የፅሁፉን አላማ ይገልጻል
የመፅሐፉን አላማ ለይ
የመፅሀፉን አጠቃላይ ሃሳብ የሚገልጽን አረፍተ ነገር መለየት ትችል እንደሆነ ፈልግ። በፈጠራ ችሎታ የራስህን መሪ ሃሳብ ለመስጠት አትሞክር። በፀሃፊው ጫማ ውስጥ ገብተህ ራስህ በተመስጦ ስጥተህ ከመፅህፉ የምታገኘውን ተመልክት እንጂ ከራስህ አእምሮ ለማመንጨት አትሞክር።
የመጽሐፉ መሪ ሃሳብ ወይም ማጠቃለያ ነጥቡ ምን እንደሆነ የሚታወቀው በተደጋጋሚ የሚገለጡትን የምንባቡ ቁልፍ ቃላት ሐረጎችና አረፍተ ነገሮች በተጨባጭ ከማየት የተነሳ ነው።
ተደጋጋሚውን ሃሳብ ካየን በኋላ መደረግ ያለበት ያንን ተደጋጋሚ ሙሉ በሙሉ እጥር ምጥን አድርጎ የሚገልጸውን ጥቅስ መፈለግ አለበት። ይህ ጥቅስ ለመጽሃፉ መሪ ጥቅስ ይሆናል።
መፅሃፉን ምዕራፍ በምዕራፍ ማጥናት
የመፅሃፉን አላማ ለማጥናትና ለማወቅ በወሰድከው እርምጃ መሰረት የምዕራፉንም መንገድ ተመልከት። የአንድ ምዕራፍ አላማ በሁለት የመመዘኛ ጥያቄዎች የተመሰረተ ይሆናል።
እነርሱም፡-
የምዕራፉ አላማ ሆኖ የተሰወደው ሃሳብ በምዕራፉ የተተኮረበት ትልቁ ነጥብ ነውን? ተብሎ መጠየቅ አለበት።
በምዕራፉ አለ የተባለው አላማ ከአጠቃላይ መፅሃፉ ዋና መሪ ሃሳብ ጋር ይያያዛልን?
አንድ ጊዜ የምዕራፉን አላማ ካገኘህ በኋላ ጠቅለል ባለ መልክ መፅሃፉን ሲታይ ያስተዋልከውን ነጥብ በማስታወሻ ደብተርህ ላይ መዝግበው። በእያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ የምትመለከተውን ቁልፍ ጥቅስ ያገኘህ ሲመስልህ መሪ ሃሳብ አድርገህ ከወሰድከው ጋር በማገናዘብ አስተያየው።
በምንባቡ ጎልተው የሚታዩ ክፍሎች
- ምንባቦች በይዘታቸው የሚያተኩሩባቸው ሁኔታ የተለያየ ይሆናል። የሚከተሉት ትኩረቶች በምሳሌነት ልንወስዳቸው እንችላለን፦
- በአንድ ትምህርት ርእስ ላይ የሚያተኩሩ
- በአንድ ሰው ላይ የሚያተኩሩ
- በአንድ ስፍራ ላይ የሚያተኩሩ
- በአንድ ድርጊት ላይ የሚያተኩሩ
- በአንድ ርዕስ ላይ የሚያተኩሩ
እነዚህ ትኩረቶች ደግሞ
1. በአንድ በተወሰኑ ጥቅሶች ስር ሊገለፁ ይችላሉ
2. በአንድ በተወሰኑ ምዕራፎች ስር ለገለፁ ይችላሉ
መሪ ሃሳብን በፈጠራና በነሲብ እንደማታመጣ ሁሉ መፅሃፉንም እንዲሁ በራስህ የሚከፋፈልበትን ሁኔታ ከራስህ አታምጣ ። ራሱ የምታነበው መፅሃፍ ይህንን ለማግኘት ይምራህ። ሁሉም መፅሃፍ የመከፋፋል ባህርይ የለውም። የመከፋፈል ፀባይ ሲኖረው ከፅሁፉ ከራሱ ይለያል።
አንድ መፅሃፍ- በቀን፣በቦታ፣በርዕስ፣ በዶክትሪን በነገሱት ነገስታት ፣በዋና ገፀባሕርያትና በዋና ዋና ክንዋኔዎች ሊከፈል ይችላል።
ለምሳሌ የሚከተሉትን መጻሕፍት ማየት ይቻላል
1. የሮሜ መፅሃፍ
i. ምዕ.1-11 ዶክትሪን
ii. ምዕ.12-16 ተግባራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።
2. የዘፍጥረት
a. ምዕ. 1-11 የዘፍጥረት መፈጠር
የሰው ውድቀት
የውሃ ጥፋት
b. ምዕ. 12-50
i. በአብርሃም
ii. በይስሃቅ
iii. በያዕቆብ
iv. በዮሴፍ ላይ ያተኩራል
የመመልከት ጥያቄዎች
በመመልከት ሂደት ጊዜ ውጤታማ ግንዛቤ እንድናገኝ ከተፈለገ ስድስት ነጥቦችን በትኩረት መመልከት አለብን።
1) ትኩረት የተሰጠባቸው ነገሮችን መለየት
መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ መንገድ ትኩረት የተሰጠባቸውን ነገሮች ያመለክታል። ትኩረት የተሰጠበት ነገርን ለመለየት በምን እናውቃለን?
1. ለነገሩ በተሰጠው የቦታ ስፋት
§ የምዕራፉ ብዛት
§ የጥቅሱ ብዛት
2. ጸሐፊው ያተኮረበትን ጉዳይ ራሱ ከገለጸልን
§ የዮሐንስ ወንጌል በምን ላይ እንደሚያተኩር ምዕ.20፥30 በግልጽ ያሳየናል።
§ የይሁዳ መልእክት በምን ላይ ያተኩራል?
3. ነገሩ የተጻፈበት ቅደም ተከተል
§ ሰውና ስራን አስመልክቶ በዘፍጥረት ላይ ከሞዕራፍ 1-3 ምን አይነት ቅደም ተከተል ትመለከታለህ?
4. ከትንሹ ወደ ትልቁ በሚሄድ ወይንም ከትልቁ ወደ ትንሹ በሚሄድ አጻጻፍ።
§ በዳዊት ሕይወት 2ኛ ሳሙኤል ከ 11-12 ያለው ታሪክ ከአጠቃላይ የዳዊት ታሪክ ጋር ሲገናዘብ ላለፈውና ለሚመጣው የሚኖረውን ሚና እናያለን።
2) የተደጋገሙ ነገሮችን ተመልከት
በዚህ ስር የምንመለከታቸው የሚደጋገሙ ነገሮች ምንድር ናቸው? ጌታ ኢየሱስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ” ሲል በመደጋገም የሰዎችን ጆሮ በማንቃት መናገሩ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ነገሮችን የሚደጋግምባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉት። የሚከተሉት ጎልተው የምናያቸው ናቸው።
1. የቃላት፤ የሐረጎችና የንዑስ አረፍተ ነገሮች ድግግሞሽን በመጠቀም።
a. መዝ. 136፥1-2
i. በዚህ ድግግሞሽ ምን እንረዳለን?
b. በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ስለ እምነት ያለው ድግግሞሽ።
i. ፀሐፊው ምን ለማለት ፈልጎ ነው ይህንን የሚደጋግመው?
2. ድርጊቶችን ደጋግሞ በመግለጽ
a. መጽሐፈ መሳፍንት
3. በታሪኮች መካከል ያለ ንጽጽር ወይንም ምስስል
a. አቤልና ቃየል
b. ዮሴፍና ወንድሞቹ
c. ሳዖልና ዳዊት
4. በአዲስ ኪዳን የብልዩ ኪዳን ጥቅሶች መጠቀሳቸው
a. በብልዩ ኪዳን የተነገረውን እውነት እግዚአብሔር ሊያተኩርበት መፈለጉን ያሳያል።
5. ቁጥርን በመጠቀም ሊገለጽ የሚፈለገው ነቀር ላይ የሚደረገ ማተኮር።
a. በሐዋርያት ስራ ቁጥር ትልቅ ድርሻ አለው።
b. በራዕይ መጽሐፍ
c. በዳንኤል
3) የተዛመዱ ነገሮችን በመለየት
የተዛመዱ ነገሮች ስንል የሚያያዙና የጋራ በሆነ ነገር ያላቸው ማለት ነው። ሁት ነገሮች ጎን ለጎን በመሆናቸው ብቻ የሚዛመዱ ናቸው ማለት አይቻልም። የተዛመዱ ነገሮችን ለመለየት ሶስት ነገሮችን መመልከት አለብን።
1. ከአጠቃላይ ወደ ዋና መሄድ
2. ጥያቄና መልስ
3. ምክንያትና ውጤት
4) የሚመሳሰሉና የማይመሳሰሉትን ነገሮች መመልከት
ንጽጽሮሽና መመሳሰል በአንድ ስነ ጽሁፍ ውስጥ ፍጥጥ ብሎ የሚታይ ይሆናል። ሊተላለፍ የሚፈለገውን መልእክት በሚያምር ውበትና ስዕላዊ ቅርጽ ያሳያል።
የሚመሳሰሉ ነገሮች የሚገለጹባቸው መንገዶች
1. የሚመሳሰሉ ነገሮች “እንደ፤እንዲሁ” በሚሉት ቃላት ይታያሉ።
ምሳሌ፡- መዝ. 42
“ዋላ ወደ ዉሃ ምንጭ እንደሚናፍቅ”
ዮሐ.3፥14
2. የማነጻጸሪያ ቃላት ሳይጠቀም በቀጥታ ሁለት ነገሮችን በማወዳደር በማስተያየት ማስቀመጥ።
ምሳሌ ፡- ዮሐንስ 15
“እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ”
የማይመሳሰሉ ነገሮችን በመጠቀም
o “ግን፤ነገር ግን” የሚሉ ቃላትን በመጠቀም
ምሳሌ፡- ማቴ.5፥22፣28፣32፣34፣39፣44
“እኔ ግን እላችኋለሁ”
ገላ.5፥22 “የመንፈስ ፍሬ ግን”
ማቴ.6፥33 “ነገር ግን አስቀድማችሁ ...”
o “እንኪያስ” በሚል ማነጻጸሪያ የተቀመጠ
ምሳሌ፡- ሉቃ.18፥7 “እግዚአብሔር እንክያስ...”
የማይጠበቅ ጥያቄ በመጠየቅ
ምሳሌ፡- ሉቃስ 8፥40-48 ታሪኩ በሙሉ በአንክሮ ሲታይ “የዳሰሰኝ ማን ነው?” የሚለው ጥያቄ የማይጠበቅ ጥያቄ ነው።
5) ለተግሳጽና ለምክር ለመበራታትም ሆነ ለእምነት ምሳሌ የሚሆኑን የቅዱሳንን የሕይወት ሁኔታ በመመልከት
1. ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረጉ
2. ኖህ ከውሃ ጥፋት ለመዳን እግዚአብሔርን ታዞ መርከብ መስራቱ
3. አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ለምሰዋት ፈቃደኛ መሆኑ
4. ሳምሶን አነሳሱና አወዳደቁ
5. ዳዊት በሐጢያት መውደቁ
የመተርጎም ጥያቄዎች
በአድን ምንባብ ውስጥ ያለውን ትክክለኛ ትርጉም ማወቅ የሚቻልበት አስተማማኝ መነገድ ጥያቄ በመጠየቅ ነው። የትርጉም ጥያቄዎች ከመመልከት ጥያቄዎች ጋር በተጓዳኝነት በመሰለፍ በሁለቱ መካከል ድልድይ ፈጣሪዎች ናቸው። የመመልከትም ሆነ የመተርጎም ጥያቄዎች በአግባቡ ከቀረበ በመመልከት የተገኘው ፍሬ ለመተርጎም ጥያቄ አጋዥ በመሆን ጥልቀት ያለው ጥናት ለማጥናት ያስችላል።
የትርጉም ጥያቄዎች በምንባቡ ውስጥ ባሉት በአራት ሁኔታዎች ላይ የተመረኮዙ ናቸው ፡-
- ቃላት (ተርሚኖሎጂ) በምንባቡ ውስጥ በጥቅም ላይ የዋሉት ቃላትን ይመለከታል። #. ቅርጽ (ስትራክቸር) የምንባቡን ሰዋስዋዊ ቅርጽና የሰነ ጽሁፉን ይዘት ይመለከታል።
- ዓይነት (ሊተራሪ ፎርም) የሰነ ጽሑፉ አገላለጽ
- የጽሁፉ መንፈስ (አትሞስፌር) የስነጽሁ ስሜት ምን ይመስላል።
የትርጉም ጥያቄ በሁለት አይነት ምድብ ሊታይ ይችላል፡-
- የትርጉሙን የተለያዩ ደረጃዎች የሚመለከቱ ጥያቄዎች
a) የፍቺ ጥያቄ (ዴፊኒሽን)(DEFINITE QUESTION )
i. ይህ ማለት ምን ማለት ነው?
b) የተስተውሎ ጥያቄ (ራሽናሌ)(RATIONAL QUESTION)
i. ለምን እንዲህ ተባለ? ለምን በዚህ ቦታ ላይ ይህ ተባለ?
c) የሚያስከትለውን የማወቅ ጥያቀ (ኢምፕልኬሽን)(IMPLICATIONAL QUESTION)
i. ይህ ምን ያመለክታል? ወዴት ይመራል? ምን ያስከትላል?
- ሁለተኛዎቹ ምድቦች የምንባቡን ዝርዝር ሃሳብ የሚመለከቱ ጥያቄዎች ናቸው፡-
i. ማንነትና ምንነትን የማወቅ ጥያቄ ጥያቄ (IDENTIFYING QUESTION )
i. ማን ወይንም ምን በዚህ ጉዳይ ይገኛል ያታያል?
1. የድርሻ ፣የተሳትፎ፣ የተካፋይነት፣የድርጊት ፈጻሚነት ወይንም የድርጊት ተቀባይነት ወይንም የድርጊት ተመልካችነት ጥያቄ።
ii. ድርጊቱ የተከናወነበት ዘዴ (ሜተድ)(MODAL QUESTION)
i. ይህ ድርጊት እንዴት ሊሆን ቻል?
iii. የጊዜ ጥያቄ (TEMPORAL QUESTION )
i. መቼ ሆነ?
iv. የቦታ ጥያቄ (LOCAL QUESTION)
i. በየት ተከናወነ?
እነዚህ ሰባት ጥያቄዎች ከአራቱ የትርጉም ጥያቄ መሰረቶች ጋር እንዴት እንደሚያያዙ የሚከተለውን ሰንጠረዥ በመመልከት ይረዳል።
የፍቺ ጥያቄ (ዴፊኒሽን) | የተስተውሎ ጥያቄ (ራሽናሌ) | የሚያስከትለውን የማወቅ ጥያቄ (ኢምፕልኬሽን) | ማንነትና ምንነትን የማወቅ ጥያቄ | ድርጊቱ የተከናወነበት ዘዴ (ሜተድ) | የቦታጥያቄ | የጊዜጥያቄ | |
ቃላት (ተርሚኖሎጂ) | |||||||
ቅርጽ (ስትራክቸር) | |||||||
ዓይነት (ሊተራሪ ፎርም) | |||||||
የጽሁፉ መንፈስ (አትሞስፌር) |
የትርጉም ጥያቄዎችን መልስ ለማግኘት የሚጠቅሙ ተጨማሪ መጻሕፍት፡-
i. የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት
ii. የቲዎሎጂ መዝገበ ቃላት
iii. ኢንሳይክሎፔድያ
iv. የቃላት ፍቺ መጻሕፍት
v. የጂኦግራፊ መጻሕፍት
vi. መጽሐፍ ቅዱስን እርስ በእርሱ የሚያጣቅሱ ማጥኛ መጽሐፍ ቅዱሳት
ምን ግዜም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን በራሱ ያለመረጃ መጻሕፍት ማንበብን የመሰለ ነገር የለም። በግድ አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያለውን ሐብት ለማግኘት በኮሜንታሪዎችና በሌሎች መጻሕፍት መደገፍ የሚመረጥ አይደለም።
ልብ በል ! በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ነገር ለመጀመሪያ የተጠቀሰበት ቦታ በጣም ጠቃሚ በመሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ነው።
መጀመሪያ የተጠቀሰ እውነት
i. ሙሉ እውነት ለማግኘት የሚረዳ ቁልፍ ነው
ii. ወደ እውነቶች ሁሉ የሚያስኬድ መንገድ ነው
iii. እውነት ደረጃ በደረጃ ሲገለጽ የሚያያዝ ሰንሰለት ነው
iv. የተገለጡ እውነቶች ሁሉ መነሻ ነው
v. በውስጡ የሚያድግና የሚበቅል የእውነት ዘር የያዘ ነው
በተግባር የማዋል ጥያቄዎች
አማኞች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ሲያጠኑ ሊጠይቁአቸው የሚገቡ ዘጠኝ ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
- ልከተለው የሚገባ ምሳሌ አለን?
- ልተወው የሚገባ ሐጢያት አለን?
- ልይዘው የሚገባ ተስፋ አለን?
- ልጸልየው የሚገባ ጽሎት አለን?
- ልታዘዘው የሚገባ ትዕዛዝ አለን?
- ላሟላው የሚገባ ሁኔታ አለን?
- በቃሌ ላጠናው የሚገባ ጥቅስ አለን?
- ልብ ልለው የሚገባ ስሕተት አለን?
- ፊት ለፊት ልጋፈጠው የሚገባ ማሳሰቢያ (ቻሌንጅ) አለን?
በተግባር ለማዋል መመልከት ያለብን
- የምናነበው ክፍል መጀመሪያ ስለ ተጻፈበት ጊዜና ሁኔታ የምናውቀው ነገር ምን አለ?
- የመጀመሪያ ሁኔታ የሚታወቅ ከሆነ ይህ እውቀት አሁን ባልንበት ዘመን ላይ ምን አይነት መልእክት ይኖረዋል?
- በዚህ ክፍል ውስጥ ምን አይነት አለም አቀፍ እውነት ተገልጸዋል?
- ይህንን አለም አቀፍ እውነት ሌላ ሰው በቀላሉ እንዲረዳው በሚያስችል ቀላል አረፍተ ነገር ልትገልጸው ትችላለህ?
- ይህ የተረዳኸው እውነት በእኛ ባሕልና የኑሮ ሁኔታ የትኛውን ጉዳይ ይመለከታል?
- ይህንን እውነት በሥራ ላይ ማዋል በአንተና በምትኖርበት ክልል ምን አይነት ለውጥ ያመጣል ብለህ ታምናለህ?
- ምን አይነት እሴተ ስርዓት እንዲኖር ይጠይቃል?
- ምን አይነት የኑሮ ልዩነት እንድናደርግ ይጠይቃል?
በተግባር ማዋል ውጤታማ እንዲሆን የሚከተሉትን አድርግ?
- ለመለወጥ ውሳኔ አድርግ
- ለለውጥ የሚያበቃ እቅድ ይኑርህ
- ያወጣኸው እቅድ በተግባር እስኪፈጸም እርምጃህን ተከታተለው።
በተግባር የማዋል ጥያቄዎች
አማኞች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ሲያጠኑ የተማሩትን በተግባር ለመተርጎም እንዲችሉ ሊጠይቁአቸው የሚገቡ ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው ፡-
- ልተወው የሚገባ ሐጢያት አለ ?
Ø ጥናቱን በጌታ ፍርሃት ካላጠናን ይህ ሊሆን አይችልም።
Ø የመንፈስ ቅዱስ ወቀሳ ሊሰማን መቻል አለበት። የጌታ መገኘት ባለብት ካጠናን ይህ ይሆናል።
Ø የተወቀስንበት ሐጢያት ጌታን የበደልንበት ያለ መታዘዝ ሐጢያት በመሆኑ የአምላካችንን ይቅርታ መጠየቅ አለብን። በጌታ ደም እንድንነጻ ጌታን በንስሐ ጸሎት መጠየቅ አለብን።
Ø የተቀስንበት ሐጢያት ከሰው ጋር ያለንን ግንኙነት ማስተካከል የሚጠይቅ ከሆነ በደንብ አስበንበትና ጸልየንበት ማድረግ ያለንን ማድረግ አለብን።
Ø መክፈል ወይንም መመለስ ያለብን ወይንም ማድረግ ያለብንን ባለማድረጋችን የተወቀስነው ሐጢያት ከሆነ ሊደረግ እንደሚገባው ያወቅነውን መልካሙን ነገር ማድረግ መቻል አለብን።
- ልከተለው የሚገባ ምሳሌ አለ?
Ø ያጠናነው ጥናት ምሳሌ አድርጎ የሚያሳየን መልካም ሕይወትና አካሄድ ካለ ያንን በተግባር ለማዋል ግዜ በመስጠት ልናጤነው ልናስበውና ለተግባራዊነቱም በተጋ ሕይወት ራሳችንን መስጠት አለብን።
Ø ያለ ጌታ እርዳታ ይህ ሊሆን ስለማይችል ጌታ እንዲረዳንና እንዲያግዘን በጸጋው ዙፋን ስር ሆነን የጌታ ባስተማረን ልንከተለው በወደድነው ጉዳይ ፀጋ እንዲሰጠን በጌታ ዙፋን ስር መሆን አለብን።
- ልይዘው የሚገባ ተስፋ አለ?
Ø ከቃሉ የተማርነው ተስፋ በመጽሐፍ ቅዱስ እውንተ ሊሄዱ ለሚወዱ ሁሉ የተሰጠ ተስፋ ነው? አንዳንዱ ተስፋ ለተወሰኑ ሰዎችና ለተወሰነ ዘመን ብቻ የሚሆን በመሆኑ በመጽሐፍ ያየነውን ሁሉ ከራሳችን ጋር ማያያዝ ስለማይኖርብን መረዳታችን የትርጉም ሚዛን የጠበቀ ሆኖ መገኘት አለበት።
Ø ጌታ በቃሉ የሚሰጣቸው ተስፋዎች ልንፈጽማቸው ከሚገቡ ትዕዛዞች ጋር የተያያዙ የሚሆኑበት ግዜ አለ።
Ø በእኛ የመታዘዝ ሁኔታ ላይ የተመሰረተው ተስፋ በተቀዳሚነት የእኛን መታዘዝ ይጠይቃል።
Ø እግዚአብሔር በሉዓላዊ ስልጣኑ ሊያደርገው የሚናገረው ተስፋ ከሆን ጌታን በመታመን ያንን ተስፋ በቋሚነት በሕይወታችን ለመጠበቅና ለመታመን እንድንችል በልባችን ልናኖረው መቻል አለብን።
- ልጸልየው የሚገባ ጸሎት አለ?
Ø መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የምናገኘው አንዱ ትልቁ ነገር ለጸልቶና ለአምልኮ መቀስቀሳችን ነው።
Ø ጌታ እንዲያደርግልን ልንለምነው የምንፈልገው ነገር ካለ እንለምናለን። የለመንነውን ለማግኘት በሚጠብቅ የእMነት መንፈስ ስለ ለመንነው በጉጉት የመጠበቅ ፀጋን እንይዛለን።
Ø የምልጃ ወይንም የምሕረት ፀሎት ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች እኝድንፀልይ የሚያነሳሳን ሁኔታ ከሆነ የተቀሰቀስንበት የፀሎት መንፈስ ሳይጠፋ ተጠብቆ በጥናቱ ቦታ ወይንም በግላችን መፀለይ መቻል አለብን።
- ልታዘዘው የሚገባ ትዕዛዝ አለ?
Ø የጌታን ቃል ስናጠና አንዱ የምናገኘው ትልቅ ነገር ቢኖር የጌታን ፈቃድ መለየትና ማወቅ መቻል ነው።
Ø በጥናታችን ወቅት የጌታን ቃል በማጥናት የተገለጠልን የጌታ ፈቃና መመሪያ ካለ የሚረዳንን የጌታ ጸጋ በመታመን ለመታዘዝ ራሳችንን እንሰጣለን።
Ø ጸጋ ባላገኘንበት ከአቅማችን በላይ ሆነው የምናገኛቸውን ሁሉ ዛሬ ካላደረግን በሚል ግልብ ስሜት ተይዘን ተስፋ እንዳንቆርጥ መጠንቀቅ አለብን። "… ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባቸው እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል" የሐዋ.15፡29 መከተል አለብን።
- ላሟላው የሚገባ ሁኔታ አለ?
Ø በመንፈሳዊ ሕይወታችን መደረግ ሲኖርበት ያልተደረገ ነገር ካለ ማድረግ ይገባናል።
Ø ልናሟላው የሚገባ ነገር መንፈሳዊ ሕይወታችንን የሚያዳብር የሚያጠናክር ለጌታም ክብር ባማረ ሁኔታ እንድንኖር የሚያደርገን ሊሆን ይቻላል።
- በቃሌ ላጠናው የሚገባ ጥቅስ አለ?
Ø የጌታን ቃል ስናጠና የምናገኛቸው የከበሩ እውነቶች የእምነት ምንጭ የሚሆኑት አድራሻቸው ልባችን ከሆነ ብቻ ነው። በልባችን ያልተሸሸገ የጌታ ቃል ምንም ለውጥ በሕይወታችን አያመጣም። (ምሳ.4፡20-23)
- ልብ ልለው የሚገባ ስሕተት አለ?
Ø የቃሉ ብርሃን በጎደለው አካሄድ ስንመላለስ ልብ ያላልነው ሁኔታ አሁን ታይቶን ከሆነ ያንን ስህተት እናርማለን። የጌታ ቃል የተገለጠ ሐጢያት ሆነው የማይቆጠሩ ነገር ግን ከጌታ ቃል ጋር የተጋጩ ብዙ ነገሮች አስተናግደን በምንኖረው ሕይወት ላይ ብርሃኑን ሲፈነጥቅልን ለስሕተታችን ምንም ምክንያት ሳንሰጥ ማረም ያለብንን ማረም ይገባናል።
- ፊት ለፊት ልጋፈጠው የሚገባ ማሳሰቢያ (ቻሌንጅ) አለ?
Ø ጌታ እኛን በመቋቋም የሚናገረን ጽኑ ነገር ካለ በጌታ ፍርሃት ራሳንን ዝቅ ማድረግ አለብን።
Ø ጌታን በመታዘዝ የምንኖረውን ሕይወት የሚያዳክምና አቅም የሚነሳ የማመቻመች ነገር እንዳለን ብናይ ያንን ለማስተካከል ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ ሆነን መገኘት አለብን።
በተግባር ልናውለው የሚገባውን እውነት አስመልክቶ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረን መጠየቅ ያለብን ጥያቄዎች የሚከተልቱ ናቸው፦
- የምናነበው ክፍል መጀመሪያ ስለ ተጻፈበት ጊዜና ሁኔታ የምናውቀው ነገር ምን አለ?
- የመጀመሪያው ሁኔታ የሚታወቅ ከሆነ ይህ እውቀት እየተጠና ባለው ክፍል ላይ ምን አይነት ግንዛቤ ያስገኛል?
- በዚህ ክፍል ውስጥ ምን አይነት አለም አቀፍ እውነት ተገልጾአል?
- ይህንን አለም አቀፍ እውነት ሌላ ሰው በቀላሉ እንዲረዳው በሚያስችል ቀላል አረፍተ ነገር ልትገልጸው ትችላለህ?
- ይህ የተረዳኸው እውነት በራስህ ባሕልና የኑሮ ሁኔታ የትኛውን ጉዳይ ይመለከታል?
- ይህንን እውነት በሥራ ላይ ማዋል በአንተና በምትኖርበት ክልል ምን አይነት ለውጥ ያመጣል ብለህ ታምናለህ?
- ምን አይነት እሴተ ስርዓት እንዲኖር ይጠይቃል?
- ምን አይነት የኑሮ ልዩነት ሊያመጣ ይችላል?
በተግባር ማዋል ውጤታማ እንዲሆን የሚከተሉትን አድርግ?
- ለመለወጥ ውሳኔ አድርግ
- ለለውጥ የሚያበቃ እምነትና ፈቃድ ይኖርህ
- የተረዳኸውን እውነት በስራ ላማዋል የምትችለው የተማርከው እውነት ልብህን ሲይዝና ውስጥህ ሲያብሰለስለው ስለሆነ እያሱ በተመከረበት ምክር ቃሉን በቀንና በሌሊት አስበው።
- የተማርከውን ለሌሎች ባማካፈል በውስጥህ ቃሉ ሊሰራ የሚችልበትን መንገድ አስፋፋ።
- በልብህ ቃሉ ከተሰወረ እምነትን ከማምጣቱም በላይ የሚሰራ ስለሆነ ከእውነት ጋር የተጣላውን ሁሉ ከአንተ ውስጥ ሊያጸዳልህ ይችላል።
- የተማርከው ቃል የሚጠይቀውን የተግባር ሕይወት ጌታን በማመንና በመፍራት በፍቅር እየታዘዝክ የኑሮህ መመሪያና መለኪያ የመንገድህ መረማመጃ ይሁንልህ።